31ኛው የህፃናት ቀን በአሶሳ ተከበረ

ሰኔ 12/2014 (ዋልታ) ለ31ኛው የህፃናት ቀን “በህፃናት ላይ የሚደርሰውን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በጋራ እንከላከል” በሚል ሀሳብ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ተከብሯል።
በርካታ ህፃናት ለተለያዩ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የሚጋለጡባት አፍሪካ ቀኑ ለ32ኛው ጊዜ ሲከበር በኢትዮጵያ ለ31ኛ ጊዜ ነው በአሶሳ የተከበረው።
በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ በሚደርሱ ችግሮች ሳቢያ ከሚጎዱ የማኅበረሰብ ክፍል ወስጥ ህፃናት ቀድሞ እና በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቂዎች ሲሆኑ በዚህ ረገድ ደግሞ አፍሪካ ቀዳሚ ነች።
ኢትዮጵያ በህፃናት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከል ከተለያዩ ተቋማት በጋራ እየሰራች ብትገኝም አሁንም ውስንነት አሉበት።
በዚህ መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ከሀገራዊ ለውጡ ተቃራኒ የቆሙ ፀረ ሰላም ኃይሎች በተለያዩ አከባቢዎች ላይ የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች ህፃናትን አየጎዳ መሆኑን አንስተዋል።
በተጨማሪም በህፃናት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን በመከላከል በኩል አሁንም ክፍተት መኖሩን አንስተው በክልሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እና በመልካም ስነ ምግባር የታነፁ ህፃናትን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኢፌድሪ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋየ (ዶ/ር) ክፉና ደጉን መለየት በማይችሉ ህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃት ለዘላቂ የስነ ልቦናዊ እና አካላዊ ጉዳቶች ይዳርገቸዋል ነው ያሉት።
ለዚህም ህጻናትን ከጥቃት መከላከል የሀሉም ግዴታ ነው ያሉ ሲሆን በኢትዮጵያ በህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች እንደመብት ሲታይ መቆየቱንም ነው ያነሱት።
ይህም የሚጀምረው ለህፃናቱ እጅግ ቅርብ ከሆኑ እንደ ወላጆች፣ አሳዳጊዎች ወይም ቤተሰቦች ነው ብለዋል።
እነዚህን ችግሮች ለመከላከል እና ለማስቆም የሚሰሩ ሥራዎች በአንድ ጀንበር ለውጥ ለማምጣት ባይቻልም በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ ሚንስትሯ ጠቅሰዋል።
ሚልኪያስ አዱኛ (ከአሶሳ)