አዲስ አበባ ሁሉን መሰብሰብ የምትችል አድርገን ልንገነባት ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

አዲስ አበባን የሚኖሩባት ሳይሆን ሁሉን መሰብሰብ የምትችል አድርገን ልንገነባት ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ለመከፋፈልና የእኔ ለማለት ከመቸኮል ይልቅ የማያግባቡ ጉዳዮችን በመነጋገር መፍታትና መጓዝ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በአለም አቀፍ ደረጃ ለ108ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ43ኛ ጊዜ እየተከበረ በሚገኘው አለም አቀፍ የሴቶች ቀን ላይ ባደረጉት ንግግር ላይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ መዲና ብሎም ሁሉን አቅ ፋና ተሸክማ የምትኖር ከተማ ናት።

ሱዳን ካርቱም በርካታ ኢትዮጵያዊያንን ፣ ኬንያ ናይሮቢም በርካታ ሶማሌያዊያንን ይዘው ይኖራሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባም ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን የመላ አፍሪካዊያን ማዕከል መሆኗን ጠቁመዋል።

ይሁንና ሁሉን ነገር ማሰባሰብ ሲቻል የሚያለያየን ከሆነ እንደዋዛ የምናፈርሰው፣ ሰብስበን የማንገነባውና ለትውልድ ዕዳ የምንጥል መሆኑን መገንዘብ ግድ ይላል ብለዋል።

በመሆኑም ባፈረስነውም ልክ የማንገነባውና ለትውልድ ዕዳ የምንጥል እንዳንሆን ኢትዮጵያ በእናት እንደምትጠራው ሁሉ እናቶች ልጆቻቸው በትጋት እንዲጠብቋት በትጋት እንዲሰሩም ጠይቀዋል።

“ኢትዮጵያዊያን እኔስ በአገሬ እንኳን ሰው ወፍ አላምዳለሁ” እንዲሉ የወፉ ይቅርብንና የራሳችን ወገን የሆነውን ኢትዮጵያዊ ማለማመድ የተሻለ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ማንኛውም ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዊ የጎረቤቱን ሰላምና አብሮነት ልክ እንደራሱ ጉዳይ ማሰብና መስራት ይኖርበታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድል ብቻ የመጋራትና ሽንፈትን የመሸሽ አባዜ እንዲወገድ ልጆችን በተገቢው መንገድ ማስተማር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በዚህም ለመከፋፈልና የእኔ ለማለት ከመቸኮል ይልቅ የማያግባቡ ጉዳዮችን በመነጋገር መጓዝ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በወጣትነት ዘመን እንዳለው ጀግንነት ማስፈራራት ብቻ ሳይሆን በአዛውንትነት ዘመን የሚመጣውን ቁጭትና ጸጸት ታሳቢ አድርገን ለጦርነትና ወንድምን ለመግፋት ያለንን ጉልበት ለሰላም፣ ለአንድነትና አብሮ ለመኖር መጠቀም ይኖርብናልም ብለዋል። (ኢዜአ)