ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የተመድ ረዳት ዋና ጸሀፊ ሆነው ተሾሙ

የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ጸሀፊ ሆነው ተሹመዋል።

የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁን የድርጅቱ ረዳት ዋና ጸሀፊ አድርገው መሾማቸውን በትላንትናው እለት ይፋ አድርገዋል።

ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ለዚህ ከፍተኛ ሃላፊነት የተሾሙት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እንዲሁም ለደርጅቱ ዘላቂ የልማት ግቦች መሳካት ላደረገችው አስተዋጽኦ ከፍተኛ የመሪነት ሚና በመጫወታቸው ነው ተብሏል።

የተመድ ውሳኔ ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን መድረኮች እስካሁን ላከናወናችው እንቅስቃሴ የተሰጠ እውቅና ሲሆን በቀጣይም ከፍተኛ አካባቢያዊና አህጉራዊ ሃላፊነት እንዳለበት የሚያመለክት ነው።
የተመድ ረዳት ዋና ጸሀፊ ቦታ በድርጅቱ ሶስተኛው ከፍተኛ የሃላፊነት እርከን ሲሆን ለዶክተር ወርቅነህ መቀመጫውን ኬንያ ናይሮቢ ያደረገውን የተመድ ዋና ጽህፈት ቤት የመምራት እና የማስተባበር ሃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።

የተመድ የኬንያ ጽህፈት ቤት አምስት ሺህ ሰራተኞችን የያዙ አስራ ስምንት ኤጄንሲዎችን የሚያስተዳድር ሃላፊነት አለው። (ምንጭ፡-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽ/ቤት)