በባሕር ዳር ማረሚያ ቤት በተነሳ ግጭት የ5 ሰዎች ህይወት አለፈ

በባሕር ዳር በማረሚያ ቤት በተፈጠረ ግጭት የ5 ታራሚዎች ህይወት ሲያልፍ ከ20 በላይታራሚዎች ላይ ደግሞ ጉዳት መድረሱ ተገለፀ።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ማረሚያ ቤት ኃላፊ ኮማንደር ውብሸት መኮንን እንደተናገሩት፥ የፀጥታ ችግሩ የተከሰተው ትናንት ከቀኑ 7፡00 አካባቢ ነው።

የችግሩ ምክንያትም “አደንዛዥ እፅ እና ሞባይል ወደ ማረሚያ ቤቱ ገብቷል” የሚል ጥቆማ ለማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች ደርሷቸው ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ታራሚዎች ውስጥ ለፍተሻ በገቡበት ወቅት የማፈን ሙከራ በመደረጉ ነው ብለዋል።

ወደ ታራሚዎች የገቡትን 6 የፖሊስ አባላትን ለማፈን ጥረት መደረጉና አምስቱ ከመታፈን ማምለጣቸውን የገለጹት ኃላፊው፥ አንደኛው የፖሊስ አባል ግን በታራሚዎች በመታፈኑ እንዲለቁት ድርድር ቢደረግም ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆኑም።

ይህንን ተከትሎ ታራሚዎች ወደ ፖሊሶች ድንጋይ መወርወር እና ጉዳት ማድረስ በመጀመራቸው የአድማ ብተና ፖሊሶችን እገዛ በመጠየቅ በአስለቃሽ ጋዝ ለማስለቀቅ እና ለማረጋጋት ጥረት ተደርጎ ነበር ብለዋል ኮማንደር ውብሸት።

በአመፁ አንሳተፍም ያሉትን ታራሚዎች አመፅ ቀስቃሾቹ ጉዳት እንዳደረሱባቸውም ኮማንደሩ ተናግረዋል።

እስከዛሬ ጥዋት ባለው መረጃም የአምስት ታራሚዎች ሕይወት ማለፉን ያረጋገጡት ኮማንደሩ፥ ቀላል እና ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ታራሚዎች ቁጥር በውል ባይታወቅም ከ20 እንደሚበልጡም አስታውቀዋል።

ታፍኖ የነበረው አንድ አባል በትናንትናው እንዲለቀቅ መደረጉ እና በሌላ አንድ የፖሊስ አባል እስካሁን አለመገኘቱን ነው ኮማንደር ውብሸት ያስታወቁት።

በማረሚያ ቤቱ ውስጥ በተደረገው ፍተሻም 20 ሞባይል ስልኮች፣ ቢላዋ፣ ጩቤ፣ ገጀራ፣ አካፋና ዶማ እንዲሁም ለማቀጣጠያነት የሚያገለግል ‹ላይተር›፣ አሲድና ሀሺሽ ተገኝተዋል፡፡

ምንጭ፦ አብመድ