የፀጥታ ችግሮች ያሉባቸው አካባቢዎች እየተለዩ ነው – ፌዴራል ፖሊስ

የፀጥታ ችግሮች ያሉባቸው አካባቢዎችን የመለየት ስራ እየተሰራ መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ዘጠነኛው የፌዴራልና የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባኤ በቢሾፍቱ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በጉባኤው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል እንዳሻው ጣሰው የፀጥታ ችግሮች ያሉባቸው አካባቢዎችን በመለየትና የችግሮቹን መንስኤ በማጥናት መፍትሄ ለማምጣት እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡

ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳዳሮች የተወጣጡ ኮሚሽነሮች በጉባሄው ላይ የ3 ወር የፀጥታ ሪፖርት በማቅረብ ላይ ናቸው፡፡

የጉባኤው ተሳታፊዎች የሚቀርቡ ሪፖርቶች፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የሪፎርም እቅድና እስካሁን ያከናወናቸው ተግባራት ቀርበው ውይይት እንደሚያደርጉም ተነግሯል፡፡

ጉባኤውም እስከ ነገ የሚቀጥል ሲሆን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅ ላይም ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡