የኢትዮ-ጅቡቲን ግንኙነት ወደ ላቀ ከፍታ ለማድረስ እሰራለሁ-አምባሳደር አብዱልአዚዝ መሐመድ

በአፍሪካ በመልካም ምሳሌ የሚነሳውን የኢትዮ-ጅቡቲ ግንኙነት ወደ ላቀ ከፍታ ለማድረስ እሰራለሁ ሲሉ አዲስ የተሾሙት አምባሳደር አብዱልአዚዝ መሐመድ ተናገሩ።

በጅቡቲ የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር በመሆን የተሾሙት አምባሳደር አብዱልአዚዝ መሐመድ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለጅቡቲው ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦመር ጌሌ  አቅርበዋል፡፡

አምባሳደር አብዱልአዚዝ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዝዳንቱ ባቀረቡበት ወቅት በጅቡቲ በነበራቸው ቆይታ ውጤታማ ስራ የሰሩትን የክብርት ፕሬዚዳንት ሳህለ-ወርቅ ዘውዴን ሰላምታ ለፕሬዝዳንቱ ያስተላለፉ ሲሆን በአህጉሪቷ ተምሳሌታዊ የሆነውን የሁለቱ አገራትን ግንኙነት ወደ ላቀ ከፍታ ለማድረስ ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ለዚህ ቦታ በመመረጣቸው ክብር እንደሚሰማቸው የገለጹት አምባሳደር አብዱልአዚዝ በደም-የተሳሰሩትን የሁለቱን አገራት ህዝቦች ፈርጀ-ብዙ ግንኙነት የላቀ እመርታ እንዲያሳይ ጠንክረው እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

አምባሳደሩ በተለይ በ15ኛው የኢትዮ-ጅቡቲ የጋራ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው የነበሩትን እንደ ኢትዮ-ጅቡቲ የጋዝ መስመር ዝርጋታ፣ በጅቡቲ የሚኖሩ የኢትዮጵያውያን የስራ-ፈቃድ ክፍያ የመሳሰሉት ተግባራት ፈጣን እመርታ እያሳዩ መሆኑን ገልጸው፤ የሁለቱ እህትማማች አገሮች ህዝቦች ችግሮቻቸውን ለመፍታት በሚያደርጉት ትግል የአገራቱ መንግስታት በጋራ የሚያደርጉት ርብርብ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ በበኩላቸው በኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር 302 አውሮፕላን ላይ በደረሰው አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን በመግለጽ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ አያይዘውም በቆይታቸው የጅቡቲ መንግስትና ህዝብ ድጋፍ እንደማይለያቸውና የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በቅርበት እንደሚሰሩ ለአምባሳደር አብዱልአዚዝ አረጋግጠውላቸዋል።  (ምንጭ፡- ኤዚአ)