በእውቀትና በስክነት መመራት እንደሚገባ ተገለጸ

በጉልበት ሳይሆን በእውቀት፣ በስሜት ሳይሆን በስክነት መመራት እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት በሀገሪቱ ውስጥ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የተሰሩ ስራዎችና ያጋጠሙ ችግሮች ላይ ያተኮረ መድረክ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አዘጋጅነት በሸራተን አዲስ እየተካሄደ ነው፡፡

መድረኩ አዲስ ወግ መርሃ ግብር የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን፥ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በመድረኩ ንግግር አድርገዋል፡፡

በንግግራቸውም ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ጎዳና ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡

ይህ ለውጥ በረከቱ እየጨመረ ፈተናዎች እየቀነሱ ለመጓዝ ምሁራንን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባልም ነው ያሉት።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ወቅቱ በጉልበት ሳይሆን በእውቀት በስሜት ሳይሆን በስክነት ልንመራና ልንመራበት የሚገባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ እውቀት መር የሆነ ማህበረሰብን መፍጠር እንደሚያስፈልግም ነው ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ባደረጉት ንግግር የገለፁት፡፡

ይህ ሲሆን ስሜታዊነት፣ መንጋነት እና ጀምላ ፈራጅነት የጥፋት እንጅ የልማት መንገድ አለመሆኑን ሁሉም በቀላሉ ሊረዳው ይችላልም ብለዋል በንግግራቸው፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ተሳታፊዎቹ አራት መሰረታዊ ነገሮችን በትኩረት እንዲሚመለከቱም አሳስበዋል፡፡

እነዚህም አብርሆት፣ የሀሳብ ልዕልና፣ የውይይት ባህልና ሂስን የማቅረብ ጥበብን ማስለመድ የምሁራን ሀላፊነት መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የአብሮሆትን አስፈላጊነት በተናገሩበት ወቅት ፕሬዚዳንቷ እንደገለፁት ምሁራን መንገድን ወለል አድርገው ማሳየት እና የእውቀት አብርሆት እንዲኖር እውቀትን ወደ ህብረተሰቡ መርጨት እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰዋል፡፡

በተመሳሳይ የሀሳብ ልዕልና አስፈላጊነትን ያብራሩት ፕሬዚዳንቷ የጉልበት የበላይነት በዚህ ዘመን ሊያበቃ እንደሚገባ አፅዕኖት ሰጥተዋል።

ውይይቱ እስከ ነገ ድረስ የሚቀጥል ሲሆን፥ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል።

(ምንጭ፡-የጠቅላይ ሚንስትር ፅህፈት ቤት)