የአርበኞች ግንቦት 7 የባሕር ዳር ውይይት ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡

አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ በባሕር ዳር ከተማ ክልል ምክር ቤት አዳራሽ በሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታና ከሕዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የጠራው ሕዝባዊ ውይይት ተቃውሞ እንደገጠመዉ የአማራ መገናገኛ ብዙሀን ድርጅት ዘግቧል፡፡

ወጣቶች ‹‹ግንቦት ሰባት የአማራ ጠላት ነው›› በማለት ውይይት በተጠራበት አዳራሽ አካባቢ ተቃውሞ እያሰሙ ነው፡፡

ንቅናቄው ለአዳራሽ ውይይቱ ተሳታፊዎችን በማስታወቂያና በመግቢያ ወረቀት መጋበዙን የውይይት ኮሚቴው አባል አቶ ዓለሙ ፈጠነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን ወጣቶች ወደ አዳራሽ በመግባት የሰቀልናቸውን ጽሑፎች አውርደውብናል፣ የራሳቸውን ጽሑፍ በመስቀልም አውከውናል›› ብለዋል አቶ ዓለሙ፡፡

ተቃውሞ እያቀረቡ የሚገኙት ወጣቶች በበኩላቸው ‹‹ግንቦት 7 የአማራን ብሔርተኝት የሚያዳክም፣ በኢትዮጵያዊነት ስም አማራን እንዳይደራጅ የሚያሴር፣ ሀገሪቱ በብሔር ፖለቲካ መወጠሯን እያወቀ አማራ ብቻ ስለኢትዮጵያ እንዲያቀነቅን የሚወተውት ፀረ-አማራ ነው›› እያሉ ነው፡፡