የአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በአጎራባች አከባቢዎች የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችን ለመቅረፍ በጋራ እንደሚሰሩ አስታወቁ

በአማራና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ የፀጥታ ችሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል የጋራ እቅድ አዘጋጅተው ስራ መጀመራቸዉን የሁለቱም ክልሎች የፀጥታ ቢሮዎች አስታወቁ፡፡

የአማራ ክልል አስተዳደር ጉዳዮች የሰላምና ደህንነት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮሎኔል አለበል አማረ እና የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደር ጉዳዮች የሰላምና የፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ ዛሬ በጋራ በባህር ዳር መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫው የሁለቱም ክልሎች ህዝቦች ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር አላቸው፤ በሀገሪቱ ለውጥ እንዲመጣ አብረው ታግለዋል ብለዋል፡፡

የክልሎቹን ግንኙነት ለማሻከር ሰሞኑን በሰሜን ሸዋ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የተከሰተው እኩይ ተግባር የሁለቱን ክልል ህዝቦች አይወክልም፤ ይህም በፖለቲካ ነጋዴዎች የተቀነባበረ ነው ያሉት፡፡

የህግ የበላይነትን ለማስከበርና የህዝቦችን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በጋራ እንደሚሰሩም አረጋገጠዋል፡፡

ከቀዬያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ መኖሪያቸው ለመመለስና ሰላምና የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ መፍትሄዎች ማስቀመጣቸዉንም ጠቁመዋል፡፡

በሁለቱ ክልሎች መካከል የተጀመረው ዘላቂና አስማማኝ ሰላም ለማስፈን የተጀመሩ ስራዎች ከሌሎች ክልሎች ጋር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ (ኢቲቪ)