የፖለቲካ ምሁራን አንድነትን ለማጠናከር ሕዝብን በሚያቀራርቡ አጀንዳዎች ላይ መስራት እንዳለባቸው ተገለፀ

በኢትዮጵያ የህዝቦች አንድነት እንዲጠናከር የፖለቲካ ምሁራን ሕዝብን በሚያቀራርቡ አጀንዳዎች ላይ መስራት እንዳለባቸው ተገለፀ፡፡

ለዋልታ አስተያየታቸውን የሰጡት ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት መሪዎች ኢትዮጵያ የታላቅ ሕዝቦችና ታሪክ ባለቤት እንደመሆኗ ይህንን ለማስቀጠል ሕዝብን በሚያቀራርቡ ጉዳዮች መድረኮችን ማዘጋጀት ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የሀገሪቱ አንድነት በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲፀና እና ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔርሰቦችና ሕዝቦች ፍትህንና ዴሞክራሲን ለማረጋገጥ መስራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝቦች በታሪክ ውስጥ አንድም የእርስ በርስ ችግር ኖሮባቸው አያውቅም ያሉት አስተያየት ሰጪዎች፣ የችግሩ ፈጣሪዎች ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ናቸው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር እና በኢኮኖሚ የተሻለ ቁመና ለማምጣት በአንድነት ላይ ያተኮሩ ተግባራት ሊከናወኑ እንደሚገባም አክለዋል፡፡