በጥናት ያልተደገፉ የታሪክ አስተምህሮዎች በሕዝቦች አንድነት ላይ እንቅፋት እንዳይሆኑ ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ

በበቂ ጥናት ያልተደገፉ እና የተዛቡ የታሪክ አስተምህሮዎች በህዝቦች አንድነት እና በሀገር ልማት ላይ እንቅፋት እንዳይሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸዉን እንዲወጡ ተጠየቀ፡፡

በኦሮሞ ህዝብ ባህል እና ታሪክ ዙሪያ የተሰሩ የምርምር ስራዎችን  ለአገራዊ  እድገት ማዋል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በመቱ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡

የመቱ ዩኒቨርሲቲም በዚሁ ረገድ ሃላፊነቱን ለመወጣት የአካባቢዉን ማህበረሰብ ቋንቋ፣ ባህል እና ወግ ለማበልጸግ የሚረዳ የባህል ማዕከል ማቋቋሙን የዩቨርሲቲዉ ምክትል ፕሬዝዳንት ተባባሪ ፕሮፌሰር ፀጋዬ በርኬሳ ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የተሳተፉ ምሁራን እንደተናገሩት በሀገሪቱ ህዝቦች፣ ባህል እና ማንነት ዙሪያ ሲነገሩ የነበሩ ትርክቶች አልፎ አልፎ የህዝቦችን እኩልነት የማያረጋግጡ ስለነበሩ ለግጭቶች መንስኤ ሲሆኑ ተስተውሏል፡፡

እንደ ምሁራኑ ገለጻ እነዚህን ሆን ተብለዉ በጥላቻ እና ለጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም የተጻፉ ትርክቶችን በማጥናትና ማስተካከል የወቅቱ ምሁራን ኃላፊነት ይሆናል፡፡

ምሁራኑ አክለው እንደገለጹት ሃገሪቱን በኢኮኖሚው ዘርፍ በማቃናት ህብረተሰቡንም የኢኮኖሚው ተጠቃሚ እንዲሆን መሰራት አለበት፡፡

እራሱን በኢኮኖሚ ያጠናከረ ህዝብ ደግሞ ባህልና ቋንቋዉን ለማሳደግ ብሎም ለማስተዋወቅ እንደሚቀለውም ነው የተጠቆመው፡፡

የኢሉአባቦር ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ለዋልታ ቴሌቪዥን በላከው መረጃ መሠረት የኦሮሞን ህዝብ አስመልክቶ ሀገራዊ እና አለማቀፋዊ ጠቀሜታ ያላቸዉ በርካታ ያልተጠኑ እሴቶች በመኖራቸዉ ምሁራንና ባለድርሻ አካላቱ በጥልቀት አጥንተዉ ለአገራዊ እድገት ማዋል እንደሚገባቸው ተገልጿል፡፡