በአማራ ክልል የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ምክክር እየተካሄደ ነው

በአማራ ክልል በተለያዩ ወቅቶች የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል የምክክር ጉባኤ እየተካሄደ ነው፡፡

በጉባኤው የተገኙት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ለችግሮች የሚመጥን የሕግ ማስከበር፣ ሕዝቡ የሚፈልገውን ሰላም ለማረጋገጥ የፌዴራል እና የክልሉ አመራሮች፣ መከላከያ እና ብሔራዊ ደህንነት ቢሮ በመገኘታቸው ለቀጣይ ስምሪት ከፍተኛ እገዛ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ሲፈጠሩ የቆዩ የፀጥታ ችግሮችን ለመገምገም ዓላማ ያደረገው ምክክሩ ለችግሩ የሚመጥን ጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራ ለመሥራት እንደሚያግዝ ታምኖበታል፡፡

የፀጥታውን ችግር ለመቆጣጠር እና ለዜጎች አስተማማኝ የፀጥታ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚደረግ ምክክር ነውም ተብሏል፡፡

ከሰሞኑ በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ አካባቢ የተከሰተውን ግጭት ለመፍታት የተደራጀ ቡድን ወደ አካባቢው ማምራቱም ተነግሯል፡፡

በዳንጉር አካባቢ የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎም በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ጃዊ አካባቢ የፀጥታ ችግር መፈጠሩ ታውቋል፡፡

(ምንጭ፦አማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት)