ጠ/ሚ ዐብይ ከብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀረሚ ሃንት ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡  

በውይይታቸው ላይም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በተመለከተ እና በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ መደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ  ዙሪያ መክረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ አካባቢ በለንደን የሚዲያ ነፃነትን በማስከበር ላይ አተኩሮ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ በመገኘት ንግግር እንዲያቀርቡም ጋብዘዋቸዋል።

ትናንት ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ የገቡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፥ ቀደም ብለው ከኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

ሚኒስትሮቹ በውይይታቸውም በሁለትዮሽ እና በቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸው ነው የተገለፀው።

አቶ ገዱ በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በለውጥና በዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ላይ የምትገኝ መሆኑን አብራርተዋል።

በዚህ ረገድ የብሪታኒያ መንግስት ለሀገሪቱ እያደረገ ላለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍም አመስግነዋል።

የአካባቢው ሰላም ከኢትዮጵያ ሰላም ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑን ያነሱት አቶ ገዱ፥ ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላም እንዲሰፍን በስፋት እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች ነው ያሉት። ከዚህ ባለፈም ከኤርትራ ጋር ስለተደረሰው የሰላም ስምምነት ገለጻ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን እና በሶማሊያ ሰላም እንዲሰፍን በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፥ ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ውህደት እንዲመሰረት ከአካባቢው ሀገሮች ጋር በቅርበትና በትብብር እየሰራች ትገኛለችም ብለዋል።

የብሪታኒያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ እያደረጉ ያለውን የኢቨስትመንት እንቅስቃሴም አድንቀዋል።

ብሪታኒያ በኢትዮጵያ በንግድ እና በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላትን ጉልህ ድርሻ አጠናክራ እንደምትቀጥል እምነታቸው መሆኑንም አቶ ገዱ አንስተዋል።

የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀረሚ ሃንት በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየወሰደች ያለውን ቆራጥ የለውጥ ሂደት ያደነቁ ሲሆን፥ ለዚህም ብሪታኒያ ሙሉ ድጋፏን ትሰጣለች ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እውን እንዲሆን ብሪታኒያ የዴሞክራሲ ተቋማትን አቅም በማሳደግ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግም አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላም እንዲሰፍን እያደረገች ያለውን ሰፊ ስራም እንግሊዝ ታደንቃለች ያሉት ሚኒስትሩ፥ ብሪታንያ በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍንም ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራቷን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

የብሪታንያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሀገሪቱ መንግስት ለባለሀብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋልም ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

ኢትዮጵያ እና ብሪታኒያ በኢኮኖሚ፣ በዲፐሎማሲ እና በባህል ዘርፍ ዘመናትን ያስቆጠረ ጥብቅ ግንኙነት አላቸው።

ብሪታኒያ በአዲስ አበባ ኤምባሲ ከከፈቱ የዓለም ሀገሮች መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ የምትሰለፍ ሲሆን፥ በተመሳሳይ ኢትዮጵያ በለንደን ኤምባሲያቸውን ከከፈቱ የአፍሪካ ሀገሮች መካከል የመጀመሪያዋ ሀገር መሆኗን መረጃዎች ያሳያሉ።