አዲስ ወግ አንድ ጉዳይ የህግ የበላይነት በዴሞክራሲ ሽግግር ሂደት በሚል ርዕስ ተካሄደ

በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አዘጋጅነት አዲስ ወግ አንድ ጉዳይ “የህግ የበላይነት በዴሞክራሲ ሽግግር ሂደት” በሚል ርእስ ተካሄደ ።

ይህ ውይይት የህግ የበላይነትን ፍልስፍናዊ፣ ሀሳባዊ፣ ህጋዊ መሰረቶች እና መነሻዎች ላይ በማተኮር የተካሄደ ነው ተብሏል፡፡

ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ እና ዶክተር ጌታቸው አሰፋ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ እና የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ንግግር አድርገዋል፡፡

የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ዜጎችን ያሳተፈ የዲሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት የመንግሥትን ቁርጠኛ መሆኑን በዚህ ውይይት ላይ ተናግረዋል፡፡

የተቋማት ሥነ ልቡናዊ አወቃቀር ፀረ ዴሞክራሲያዊነት ያዘነብልበታል ያሉት ሚኒስትሯ ይኽንን መቀየር ትልቅ ሥራና ጊዜ እንደሚፈልግ አንሥተዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ የሕግ የበላይነትን ፍልስፍና መሠረቶች፣ በለውጡ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዙሪያ የተገኙ ስኬቶችና ተግዳሮቶች ዙሪያ ሃሳብ አቅርበዋል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ይህ የሽግግር ወቅት መንግሥት ሕግን ለራሱ ጥቅም ከማዋል ይልቅ የሕግ የበላይነትን ወደ ተቋማዊነት ማሸጋገር ያስፈልጋል ብለዋል።

ፕሬዚዳንቷ ኢትዮጵያ ሰላምና ደኅንነትን በማስጠበቅ ያስመዘገበችውን እመርታ አንሥተዋል፡፡

ሌላኛው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር ዶክተር ጌታቸው አሰፋ በበኩላቸው በሕግ መግዛት እና በሕግ መምራት መካከል ያለውን ልዩነት መገንዘብ ከየት መጣን? የትስ ነን? የሚለውን መረዳት እንደሚያስፈልግ በውይይቱ ወቅት ተናግረዋል።

ሁለተኛው አዲስ ወግ ውይይት የህግ የበላይነት በዴሞክራሲ ሽግግር ሂደት ላይ ትኩረት በማድረግም ንድፈ ሀሳባዊ፣ ፖለቲካዊ እና ነባራዊ ትርክቶችን እና ሁኔታዎችን የዳሰሰ ነው።