ም/ጠ/ሚኒስትር ደመቀ ከፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ጋር በቀጠናዊ ትብብርና በሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ መከሩ

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ ጋር በቀጠናዊ ትብብር እና በሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ በኢንቴቤ መክረዋል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራ ልዑክ ወደ ኡጋንዳ ያቀና ሲሆን፣ መሪዎቹ ባደረጉት ምክክር በተለያዩ መስኮች ለረጅም ዓመታት የዘለቀው የኢትዮጵያ እና የኡጋንዳ የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መግባባት ላይ ደርሰዋል።

ሁለቱ ሃገራት በቀጠናው ዙሪያ በሚስተዋሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይም በመወያየት ትብብራቸውን ለማጥበቅ በሚችሉበት አግባብ ዙሪያ ተስማምተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ በመጨረሻም ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተላከውን የትብብር መልዕክትም ለፕሬዚዳንት ሙሴቪኒ ማስረከባቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡