ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ኃላፊ ሌተናል ጀኔራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ጋር ተወያዩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ኃላፊ ሌተናል ጀኔራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ጋር ተወያዩ፡፡

ጀነራሉ አዲስ አባባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን የሱዳን ጊዜያዊ ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ሃላፊ ሆነው ከተሾሙ በኋላ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ጉብኝታቸውን ለማድረግ ነው አዲስ አበባ የገቡት፡፡

ጄነራሉ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጋር በነበራቸው ውይይት ሱዳን አሁን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ አብራርተዋል፡፡

በአገራቸው ከተቃዋሚ ሀይሉ አሊያንስ ፎር ፍሪደም ኤንድ ቼንጅ ፓርቲ ጋር እና ሌሎች ተቃዋሚ ሀይሎች ጋር በጋራ በመሆን በአገሪቱ ሁኔታ ዙሪያ በመመካከር እየሰሩ እንዳሉ ለዶ/ር ዐብይ ገልፀዋል፡፡

ትኩረታቸውን በሱዳን ፍትሀዊ የስልጣን ክፍፍል ዙሪያም እየሰሩ እንዳሉ ገልፀዋል፡፡

ከኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ ሂሩት ዘመነ ያገኘነው መረጃ እንሚያሳየው ኢትዮጵያ ለሱዳን ሰላም እና መረጋጋት ያለምንም ጣልቃ ገብነት በሀሳብ ድጋፍ እንደምታደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ መናገራቸውን ነው፡፡

ዶ/ር ዐብይም የሱዳኑ የሽግግር መንግስት ሁሉንም የፖለቲካ አካላት አካታች በሆነ መንገድ ማስተናገድ አለበት ብለዋል፡፡

ጀኔራሉ ወደ አዲስ አባባ ከመድረሳቸው በፊት በግብፅና በደቡብ ሱዳን ጉብኝት ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡