ኮሎምቢያ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ልትከፍት ነው

ኮሎምቢያ በአፍሪካ 7ኛ ኤምባሲዋን በኢትዮጵያ ለመክፈት ዝግጅት እያደረገች መሆኗን አስታውቃለች።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ፣ የአሜሪካ፣ የኢስያ እና የባለ-ብዙ ወገን ጉዳዮች ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ማህሌት ኃይሉ በኮሎምቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ፣ የኢስያ እና ኦሽኒያ ዳይሬክተር አልፌርዶ ራሞስ ጎንዛሌዝ ጋር በሁለትዮሽና ኤምባሲውን ለመክፈት በሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች ዙሪያ ዛሬ ተወያይተዋል።

አምባሳደር ማህሌት በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ሁለቱ አገራት የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ትብብር አላቸው።

የአፍሪካ ህብረት፣ የመንግስታቱ ድርጅት የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን፣ የበርካታ አገራት ኤምባሲዎችና ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ በሆነችው ኢትዮጵያ ኮሎምቢያ ኤምባሲዋን ለመክፈት ማቀዷ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑንም ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሌሎች የሚመለከታቸው አካለት ጋር በመሆን ለኤምባሲው በአፋጣኝ መከፈት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ለዳይሬክተሩ ገልጸውላቸዋል።

በኮሎምቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ፣ ኢስያ እና ኦሽኒያ ዳይሬክተር አልፌርዶ ራሞስ ጎንዛሌዝ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ሰፊ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች የሚካሄዱባትና ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት የምታስመዘግብ አገር በመሆኗ መንግስታቸው ኤምባሲ ለመክፈት መወሰኑን ተናግረዋል።

የኤምባሲው መከፈት የአገራቱን ግንኙነት በሁሉም ዘርፎች የበለጠ እንዲጠናከር እንደሚያስችል እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የኮሎምቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማድረግ እንደሚመጡና የሁለትዮሽ የፖለቲካ ምክክር ለማድረግ እንደሚፈልጉም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከኮሎምቢያ ጋር ያላትን ግንኙነቶች የምትከታተለው ብራዚል በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩል ነው መረጃ ያገኘነዉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነዉ።