ኢትዮጵያና ኬንያ በቱሪዝም ዘርፍ በጋራ ለመስራት በሚያስችሏቸዉ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ

የኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ ገዱ አንዳርጋቸዉና የኬንያ አቻቸዉ ሞኒካ ጁማ የሁለቱን ሀገራት የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግና የህዝብ ለህዝብ ግንኙትን ለማጠናከር በሚያስችሏቸዉ ጉዳዮች ላይ ዛሬ በአዲስ አበባ መምከራቸዉን የዉጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ፡፡

ሞኒካ ጁማ እንደተናገሩት ሁለቱ ሀገሮች ያላቸዉን ጠንካራ የፖለቲካ ግነኙነት በኢኮኖሚ፣ በንግድና በቱሪዝም ዘርፍ ማዳበር የሚያስችል አቅም መኖሩን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸዉ ገልጸዋል፡፡

በተለይ በቱሪዝም ዘርፍ ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪዝም መዳረሻ አቅምን እንዲሁም ኬንያ ያላትን የባህር ዳርቻ የዳበረ የቱሪዝም ልምድ በማጣመር በጋራ ቢሰሩ ዉጤታማ እንደሚሆኑ ገልፀዋል፡፡

የኬንያ በጋራ የመስራት ሃሳብም በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት አግኝቷል፡፡

ሚኒስትሮቹ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባም መክረዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ በቀን 6 ጊዜ የሚደረገዉ በራራ የሁለቱ ሀገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ከፍተኛ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን ይህንንም በወጣቶችና በተማሪዎች ልዉዉጥ መመስረት እንደሚገባ ተስማምተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ተማሪዎች በኬንያ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የኬንያ ተማሪዎች በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩበት ሁኔታ እንደሚመቻችም ተነጋግረዋል፡፡