አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት ጋር ተወያዩ

የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር አቶ ገዱ እንዳርጋቸው ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በሱዳን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እና በቀጣናው የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ሃሳብ ተለዋውጠዋል።

አቶ ገዱ በቅርቡ በሱዳን የፖለቲካ ሃይሎች መካከል ተፈጥሮ በነበረው አለመግባባት ለማርገብና በአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች የሰላም ድርድር እንዲቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ወደ ካርቱም በማቅናት እንዲሁም በእርሳቸው በኩል በተሰየሙት አምባሳደር ሞሃመድ ድሪር በኩል ስለተደረገው ጥረትና ስለተገኘው ገንቢ ውጤትም ለሊቀ-መንበሩ ገለጻ አድርገውላቸዋል።

በተጨማሪም በደቡብ ሱዳን የሰላም ሂደት የመከረውን 68ኛውን የኢጋድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሮች ስብሰባ ዙሪያ የተወያዩ ሲሆን፣ ምክር ቤቱ ለሱዳን ሰላም መመለስ የኢትዮጵያን ጥረት መደገፉን አብራርተውላቸዋል።

የአፍሪካ ህብረት በሱዳን ሰላምን ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተል ልዩ መልዕክተኛ መሰየሙ ይታወሳል። መረጃው የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ነው፡፡