ክስተቱ አደገኛ በመሆኑ ሁሉም ሊያወግዘውና ሊታገለው ይገባል

ከሰሞኑ በባህርዳር የተከሰተው ድርጊት የህዝቡን ታሪክ የማይመጥንና ያለፍነውን የመጠፋፋት ባህል ዳግም ወደኋላ የመለሰ አደገኛ ክስተት በመሆኑ ሁሉም በነቂስ ሊያወግዘውና ሊታገለው ይገባል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በተደረገው የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች አስከሬን ሽኝት ባደረጉት ንግግር፤ ከሰሞኑ በባህርዳር የተሰተው ጥቃት በህይወትና ማህበራዊ ገጽታው ለተጎጂዎችና ለቤተሰቦች ለትግል አጋሮቻቸው እጅግ የከበደ ነው።

ድርጊቱ የህዝቡን ታሪክ የማይመጥን በጭካኔ የታጀበ አረመኔያዊ ድርጊት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሃገሪቷ ከስልጣንና ጋር በተያያዘ የነበሩ የመጠፋፋት ባህሎች ዳግም ወደ ወደኋላ የመለሰ አደገኛ ክስተት በመሆኑ ሁሉም በነቂስ ሊያወግዘውና ሊታገለው ይገባል ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የክልሉን ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመፍታት በጋራ ዓላማ ተጋምደው፣ በአመራር ቋንቋ ተላምደው፣ በጓዳዊ አስተሳሰብ ተራምደው፤ በሙሉ ተስፋ የተሰለፉትን የቁርጥ ቀን ልጆች በእንዲህ ዓይነት ጭካኔ ማጣት ለሁሉም የላቀው ፈተናና ጸጸት ነው ብለዋል።

በመሆኑም መንግስትና መሪ ድርጅቱ ከህዝብ ጋር በመሆን ድርጊቱን ማውገዝ ብቻ ሳይሆን፤ የተሰውትን ጀግኖች ዓላማና በዘመን የማያልፍ አበርክቶቻቸውን ዳር እንዲደርስ ሁላቸንም በጽናት መጓዝ፣ መራመድና ማሳካት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።

በአገርና በክልል የተያዘውን የለውጥ አጀንዳ አጠናክሮ ለመቀጠል ዋነኛ ስራም የህግ የበላይነት በማስከበር ሰላምን በመገንባትና የኢኮኖሚ ማነቆዎቸን በመፍታት ልማቱን ማፋጠን ይገባል ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ነገር ግን እኝህ ወሳኝ ስራዎችና ሌሎች አጀንዳዎችን ለመፈጸም ብዙ እድሎች እያሉ፤በተግባር ከእድሎቻችን እየራቅን የችግሮቻችነን እድድሜ እያራዘምን እንገኛለን ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ አዙሪት ለመውጣት ከስሜታዊነት፤ ከጀብደኛነት፤ ከግለኝነትና ራስን ብቻ ከማዳመጥ ወጥተን ወደ ከፍታ የሚወስዱንን ጥበቦች መከተል ማለትም ምክንያታዊነትን፤ በሌላው ጫማ ላይ ሆኖ ማሰብን ህግና ሰርዓትን ማክበርን አርቆ ተመልካችነትን መላበስ ይኖርብናል ብለዋል።

የአማራ ክልል ህዝብም ከዚህ አኳያ ታሪኩን የሚመጥን ምህዋር ላይ በመሳፈር በውስጡ አቃፊነቱን በመላው ዓለም ላይ ተከባብሮ ሰፍቶና ሞልቶ የመኖር ባህሉን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።

ከዚህ ውጪ የሚራመዱ ሃሳቦችና አስተምሮዎች ህዝባችንን ከከፍታው የሚያወርዱት መሆኑን አውቆ በጥንቃቄ ሊያቸውና ሊመክታቸው ይገባልም ነው ያሉት።

በባህርዳር ከተማና አካባቢዋ የባሰ ጉዳት እንዳይደርስና እንዳይከሰት በሂደትም በቁጥጥር ስር እንዲውል ላደረጉ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የጸጥታ አካላትና የመንግስት አካላት ምስጋናቸውን አቅርበው፤ እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ህግና ስርዓት እንዲነግስ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በህይወት ያጣናቸው ወንድሞቻችን፤ ጀግኖቹ! ለቤተሰቦቻቸው ተገቢውን ጊዜ ሳይሰጡ፤ ስለመጪው ሀይወታቸው ሳያስቡ፤ በተለያዩ አጀንዳ ውስጥ ሆነው በድንገት ወድቀዋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሟች ልጆቻቸውም ሆነ የቤተሰቦቻቸው ተስፋ ከቶውንም ቢሆን ሊጨልም አይገባውም ብለዋል።

የክልሉ ህዝብ፣ መንግስትና የለወጥ አጋሮች ከጎናችሁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

ለሀገር አቀፍና ለክልል አቀፍ ተልዕኮዎች መሳካት ከልጅነታቸው እስከ ህልፈተ ህይወታቸው ሲሰሩ የነበሩ የመከላከያ የጦር መኮንኖች ህልፈትና በስራ ላይ እያሉ ህይወታቸው ላለፈው የድርጅታቸው ከፍተኛ አመራሮች ህልፈት የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል።