የተፈጠረው የፀጥታ ሁኔታ በክልሉ ሠላም ላይ ዘላቂ ችግር በማይፈጥርበት ሁኔታ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጸ

የተፈጠረው የፀጥታ ሁኔታ የሥነ-ልቦና ተፅዕኖ ሊፈጥር ቢችልም በክልሉ ሠላም ላይ ዘላቂ ችግር በማይፈጥርበት ሁኔታ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በወቅታዊ የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ ላይ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል፡፡

መግለጫውን የሰጡት የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ሚዲያ ልማት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ሰዒድ አህመድ ‹‹አሁን ያለው የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ ሠላማዊ፤ ችግሮች ቢፈጠሩ እንኳን የፀጥታ ኃይሉ በቁጥጥር ስር ማዋል በሚችልበት ደረጃ ላይ ነው›› ብለዋል፡፡

አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ የፀጥታ ስጋቶችና ችግሮች አጠቃላይ የክልሉን የፀጥታ ሁኔታ እንደማይገልጹትም ነው ኮሚሽነር ሰዒድ የተናገሩት፡፡

‹‹የተፈጠረው ችግር ድንገተኛነትና ያልተለመደ መሆን በኅብረተሰቡ ሥነ-ልቡና ላይ ችግር የፈጠረ ቢሆንም ሕዝቡ አመዛዛኝ በመሆኑ በፍጥነት ከችግሩ መውጣት ተችሏል›› ነው ያሉት፡፡

የክልሉ ሕዝብ ለአካባቢው ሠላም ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን በመግለጫቸው ያነሱት ኮሚሽነር ሰዒድ ‹‹በተለይም ወጣቱ ትናንት የነበረውን የክልሉን ከፍተኛ መሪዎች የቀብር ሥነ-ስርዓት በሠላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ያደረገው ድጋፍ ከፍተኛ በመሆኑ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ ምሥጋና ያቀርባል›› ብለዋል፡፡

በቀጣይም ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ በየደረጃው የሚገኙ መደበኛ ፖሊሶች፣ የተደራጁ የወንጀል መከላከልና መቆጣጠር አባላት እንዲሁም ሌሎች የፀጥታ አካላት ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ከአሁን በፊት ከነበረው የሰላም ማስከበር ስራ በተለያ ሁኔታ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግ ጠቁመዋል። (ምንጭ፡-አማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት)