የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብርና አረና መድረክ በክልሉ መንግስት ጥቃት እየደረሰብን ነው አሉ

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብርና አረና መድረክ በመቐለ ከተማ በአመራሮቻቸውና አባላቶቻቸው ላይ አካላዊ ጥቃት የደረሰባቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ፓርቲዎቹ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደገለፁት፤ በትግራይ ክልል በነፃነት እና በሰላም ለመንቀሳቀስ አልቻልንም ብለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በአባላቶቻቸው ላይ በክልሉ መንግስት ዛቻና ማስፈራርያ እየደረሰባቸው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የአመራር አባላት ወቅታዊ የፓርቲዎቻቸውን እንቅስቃሴ በተመለከተ እንደገለፁት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአመራሮቻቸው፣ በአባሎቻቸው እና በደጋፊዎቻቸው ላይ የሚደርሰው አደጋ እየበዛ መጥቷል፡፡

የሁለቱ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አመራሮች እንደገለፁት፤ በእነ ጄነራል ሰዓረ መኮንን የቀብር ስነስርዓት ላይ ለመገኘት መቐለ ከተማ በሄዱበት ወቅት በአመራሮቹ ላይ የግድያ ሙከራ እንደተደረገባቸው አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ በሰላማዊ መንገድ በመታገል ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በሀገሪቷ እንዲሰፍን እየሰራን እንገኛለን የሚሉትና በዚህም አካሄድ ዘመናትን አስቆጥረናል ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ፤ይሁን እንጅ ይህን ዓላማችንን እንዳንፈፅም በክልሉ መንግስት የተለያዩ ጉዳቶች እየደረሱብን ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪም ደጋፊዎቻቸው ዴሞክራሲያዊ መብታቸዉን እንዳይጠቀሙ እየተደረገ ይገኛልም ነው ያሉት ፡፡

በክልል በተለያዩ ከተሞች ወረዳዎች እና ቀበሌዎች በመዘዋወር የፖለቲካ ዓላማዎቻቸዉን ለህዝብ እያስተዋወቀቁ እንደሚገኙ የሚናገሩት የትግራይ ዴሞክራሳዊ ትብብር እና የአረና መድረክ አመራሮች ከፊታችን ሃምሌ ወር ጀምሮም ተዋህደው እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር እና የአረና መድረክ በሀገሪቷ ውስጥ ከሚገኙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡