በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ቀጣዩ የመንግስት ትኩረት ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ

በኢትዮጵያ የሚስተዋለውን ግጭት እና አለመረጋጋት በማስወገድ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ቀጣዩ የመንግስት ዋነኛ ትኩረት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግስትን የ2011 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት በትርምስና አለመረጋጋት ውስጥ ሆኖ የተሳካ ሀገር ግንባታ ማድረግ ስለማይቻል አለመረጋጋቱን በማከም ህዝቡ ወደ ሰከነ ህይወት እንዲመለስ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡  

በመሆኑም የሰላም መታጣት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት፣ ዘላቂ መፍትሄ በመስጠት እና ፖለቲካውን ወደ ተረጋጋ ውይይትና ክርክር በመቀየር የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

በቀጣይነትም የህግ አስፈጻሚ አካላትን ተቋማዊ ብቃት ለማሳደግ በሰው ሃይልና ቴክኖሎጂ በመገንባት አስተማማኝ ሰላም የማስፈን ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

በዚህ አግባብ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ በየትኛውም የሀገሩ ክፍል በማንነቱ ሳይገለል የሚኖርበት፣ ሃብት የሚያፈራበት እና ዘላቂ ህይወቱን ያለስጋት የሚመራበት ተግባራት በስፋት ተጠናክረው እንዲቀጥሉም አስታውቀዋል፡፡

የኢኮኖሚ ምርታማነትን ማሳደግና የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን ማረቅ ሌላኛው የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዘርፍ በትኩረት ካልተሰራ ከቁጥጥር ውጭ የወጣ የዋጋ ግሽበት፣ የእድገት መቀጨጭ እና ተያያዥ ቀውሶች ሊያስከትል እንደሚችል ዶ/ር ዐቢይ አስረድተዋል፡፡

የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ከባዱ ፈተና ስራ አጥነት እንደሆነ ጠቅሰው በሚቀጥሉት ወቅቶች የልማትና እድገት መመዘኛ ከፈጠሩት የስራ እድል አንጻር እንደሚታይ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ ጊዜያት የቱሪዝም መስህብን ለማሳደግ ሰፋፊ ተግባራት እንደሚከናወኑና ያሉትን የቱሪስት መዳረሻዎች ከመጠገን እና ለጎብኝዎች ምቹ እንዲሆኑ ከማድረግ ባሻገር ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለመፍጠር ይሰራል ብለዋል፡፡

ብሄራዊ ቤተመንግስትን ለጉብኝት በሚሆን መልኩ አመቻቶ ለጎብኝዎች ክፍት የማድረጉ ስራ በመስከረም 2012 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅም ገልጸዋል፡፡

የመጭው በጀት ዓመት ሌላኛው የመንግስት ትኩረት በውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ላይ ሲሆን የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴው ማዕከል የብሄራዊ ጥቅም እና የዜጎችን ክብር ማስጠበቅ ይሆናል ብለዋል፡፡

አካባቢ ጥበቃን በተመለከተ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሳተፍበት እና 200 ሚሊዮን ችግኞች በአንድ ጀንበር የሚተከልበት የአረንጓዴ አሻራ ቀን የፊታችን ሃምሌ 22፣ 2011 እንደሚከናወን ታውቋል፡፡