የውጭ ግንኙነታችን ዋነኛ ማጠንጠኛ ዜጎቻችን ናቸው – ጠ/ሚ ዐቢይ

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ዋነኛ ማጠንጠኛ ዜጎቿ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግስትን የ2011 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት የውጭ ግንኙነት እንቅስቃሴው የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ፣ ዓለም አቀፍና ክልላዊ ሁኔታን በሚያንጸባርቅ መልኩ የዜጎችን ክብር፣ መብት እና ጥቅምን በሚያስከብር መልኩ ተከልሷል፡፡

በየክፍለ አለማቱ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን በማጠናከር የዜጎችን ደህንነት እና ክብር ለማስጠበቅ ጥረት መደረጉንም አስረድተዋል፡፡ በዚህም መሰረት በተለያዩ አገራት የታሰሩ ከ15 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ተፈተው ወደ ሃገራቸው ገብተዋል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በተለያየ ምክንያት የስራ ውላቸው የተቋረጠ ከ76 ሺህ በላይ ዜጎች ያለ እንግልት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን አስታውሰዋል፡፡

የውጭ ግንኙነት ጥረት ከዜጎች በመቀጠል በዋናነት በጎረቤት ሃገራት ላይ ያተኮረ እና ሁሉንም ጎረቤት ሃገራት ያማከለ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡

በተለይ ከኤርትራ ጋር የነበረን የጦርነት ጥላ ያጠላበት ድባብ ወደ ሰላማዊ አየር ለመቀየር ሰፊ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በኬንያ እና ሶማሊያ፣ በጂቡቲ እና በኤርትራ፣ በደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ሃይሎች መካከል ሰላምን ለመፍጠር ኢትዮጵያ የድርሻዋን እየተወጣች ነው ብለው አሁን ደግሞ በሱዳን ሰላምን ለማምጣት ቀጣናዊ የመሪነት ሚናን ለመወጣት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በሌላም በኩል ለክፍለ አህጉራዊ እና አህጉራዊ ሰላም እየተሰራ ሲሆን በተለይ በቀይ ባህር ላይ ክፍለ አህጉራዊ የጋራ የቀይ ባህር አካባቢ ፖሊስ እንዲኖር ጥረቶች መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ዋነኛ የንግድ መተላለፊያ በሆነው ቀይ ባህር የባህር ላይ ውንብድና፣ ሽብርተኝነት እና የታጠቁ ሃይሎች እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር የባህር ሃይል ማቋቋም አስፈላጊ በመሆኑ የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡

በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ረገድ ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ኢትዮጵያ ከተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት ለኢኮኖሚ ማሻሻያ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማግኘቷን ተናግረዋል፡፡

የልማት አጋር ሃገራት ከሚያደርጉት የእርዳታ እና የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪም የእዳ ስረዛ እንዳደረጉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸው፣ ካልተለመዱ የብድርና የእርዳታ ምንጮች በተገኘው ድጋፍ የተመናመነውን የውጭ ምንዛሬ ይዞታ ለማሻሻል ጥረት መደረጉን አስረድተዋል፡፡