ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ በሱዳን ጉዳይ ላይ ተወያዩ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ዋና ፀሃፊ ሙሳ ፋቂ መሃመት በሱዳን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይታቸውም የአፍሪካ ሀብረት ሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት የሱዳን የፖለቲካ ሀይሎች ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት እያሳዩት ያለውን ጥረት ማድነቃቸውን ውይይቱን ተከትሎ የወጣ መግለጫ አመላክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ዋና ፀሃፊ ሙሳ ፋቂ መሃመት አክለውም እስካሁን ያለው ሂደት አስቸጋሪ ቢሆንም የኢትዮጵያ ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር መሃሙድ ድሪር እና የአፍሪካ ህብረት ልዩ መልእክተኛ ሃሴን ኤል ለባት እስካሁን ላከናወኑት ስኬታማ ስራም እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

በተጨማሪም በአፍሪካ ህብረት እና በኢትዮጵያ አማካኝነት እየተካሄደ ላለው ድርድር የሱዳን ህዝብ፣ የፖለቲካ እና የማህበራዊ ተዋናዮች ላሳዩት በጎ ምላሽም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በቀጣይም የሱዳን ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ የፖለቲካ ሀይሎችም ይሁን የማህበራዊ ዘርፍ ተዋናዮች በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ልዩነቶቻቸውን በመፍታት ፖለቲካዊ መግባባት ላይ በፍጥነት እንዲደርሱም መልእክት አስተላልፈዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የተጀመረው የሰላም ሂደት ከግብ እንዲደርስ እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።