የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ የተጀመረውን ለውጥ ያለምንም ማወላወል እናስቀጥላለን – የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ በሰጠው መግለጫ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ የተጀመረውን ለውጥ ያለምንም ማወላወል እንደሚያስቀጥል አስታወቀ፡፡  

የአማራ ክልል ሕዝብ በሕግ የበላይነት አጥብቆ የሚያምንና የሚታወቅበት እሴቱ ሆኖ መቆየቱ የሚታወቅ ነው፡፡ ‹‹ነፃነትና ፍትሐዊነት ተጓሏል›› ብሎ ባመነባቸው ዘመናትም ይህንኑ እሴቱን ጠብቆ የታገለ ሥልጡን ሕዝብ ነዉ፡፡
አማራ ‹‹በሕግ ከተወሰደች በቅሎዬ ያለ ሕግ የተቀማች ጭብጦዬ›› በሚል ብሒል የተገነባና ‹‹በሕግ አምላክ›› ሲሉት ከምንም ዓይነት ድርጊት የሚቆጠብና በሥርዓት በተሠራለት የአደባባይ ሸንጎና የፍትሕ ተቋም ብቻ ፍትሕን የሚቀበል ሕጋዊ ማንነትን የተላበሰ ሕዝብ ነው፡፡
ሕግ ሲጣስ፣ ፍትሕ ሲጓደል፣ ሰው ሲበደል እንዲስተካከል ለመንግሥት አቤት ይላል፤ እንዲስተካከል ይታገላል፤ ሲታገልም ኖሯል፤ ውጤትም አምጥቷል፤ እንጅ ሕገ ወጥነት መገለጫው ሆኖ አያውቅም፤ ሕገ ወጥ ልጅም ወልዶ አላሳደገም፤ አፈንጋጭ ካለም ቆንጥጦ ማረሙን ያውቅበታል፡፡
የሕይወት መስዋዕትነትም ጭምር ከፍሎ በትግሉ ያመጣዉ ለውጥ እንዲሆን የሚፈልገዉም ከምንም ነገር በላይ የሕግ የበላይነት የተረጋገጥበት፣ ነፃነቱ የተጠበቀበትና በዚህ ማዕቀፍ ፍትሐዊነት በሁለንተናዊ ዘርፍ እየሰፈነ እንዲሄድ ብቻ ነዉ፡፡
ከዚህ ዉጭ የተለየ ፍላጎት የሌለዉ ሕዝብ ነው፡፡ ከምንም በላይ ሥርዓተ አልበኝነትንና ሕግ ወጥነትን የሚሸከምበት ትክሻ የሌለውና በላቡ ጥሮና ግሮ የሚኖር፣ የማይገባውን የማይጠይቅ ኩሩ ሕዝብ ነው፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትም ከዚህ ሕግና ፍትሕን አዋቂ የመልካም እሴት ባለቤት ሕዝብ የተወለደና ይህንኑ አጽንቶ የሚቀጥል እንጅ በሕግ የበላይነት መከበር ጉዳይ ላይ ከማንም ጋር አይደራደርም፡፡
ለውጡ በፈጠረው የሐሳብም ሆነ የአካሄድ መደበላለቅ የተከሰቱ ክፍተቶችን ፈጥኖ በማረምና ሁሉንም በሕግና በሥርዓት አግባብ ብቻ በማስተካከል የጎደለውን እየሞላን፣ የጎበጠውን እያቀናን ወደፊት ብቻ እንጓዛለን፡፡
የአማራ ክልል የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉበት፣ የሕግ የበላይነት ያለምንም መሸራረፍ የተረጋገጠበት እንዲሁም ሕዝብና መንግሥት ተግባብተው በእጅና ጓንትነት የሚቀጥሉበት የሠላምና የፍትሕ ምሳሌ እንዲሆን በጽናት እንሠራለን፡፡
የተፈጠረው አሳዛኝ ክስተትም ቁጭት ፈጥሮብን የወንድሞቻችንን መስዋዕትነት የሚመጥን ሕዝባዊ ሥራ እየሠራን ዓላማቸውን ዳር እናደርሳለን እንጅ በሞታቸው ተደናግጠን ከጉዟችን አንደናቀፍም፡፡
የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ የተጀመረውን ለውጥ ያለምንም ማወላወል እናስቀጥላለን፡፡
ሰኔ 27 ቀን 2011ዓ.ም 
ባሕር ዳር