ህገመንግስቱ ክልል የመሆንና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የግልጽነት ችግር አለበት ተባለ

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በጋራ ባዘጋጁት የክልል ምስረታ ጥያቄ እና ህጋዊ ሂደት ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አካሂደዋል።

በውይይቱም በኢትዮጵያ የሚነሱ የክልልነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት በህገመንግስቱ  ክልሎችን መሰረት አድርጎ የተደነገገው ሕግ የግልጽነት ችግር እንዳለበት ተገልጿል፡፡

በአገሪቱ ክልል የመሆንና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ ህገመንግስቱ ምን አንድምታ አለው? የሌሎች አገራት ተሞክሮስ ምን ይመስላል? የሚሉ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበውም ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ጥናት ያቀረቡት ዶክተር ዘመልዓክ አየለ፤ ክልሎች እንዴት ሊፈጠሩ ይችላሉ? በሚለው ላይ ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎችን በምሳሌነት በማንሳት አቅርበዋል።የቀረበውን ጥናታዊ ጽሁፍ ተከትሎ በተደረገው ውይይት፤ በበርካታ የዓለም ሀገራት የክልልነት ጥያቄ ሲነሳ ኮሚሽን አቋቁሞ ጥናት በማካሄድ፣ የህገ መንግስት ማሻሻያ በማድረግ እና ህዝበ ውሳኔ በማድረግ ምላሽ እንደሚሰጥ ተሞክሮዎችን አንስተዋል፤ ተወያዮቹ፡፡

በውይይቱ ላይ የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡ ምሁራን የክልል ምስረታ ጥያቄ በተናጥል ሊወሰን አይገባም ያሉ ሲሆን፤ ሁሉንም አሳታፊ መሆን እንዳለበት አክለው ገልፀዋል።

በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሚነሱ የክልል ምስረታ ጥያቄዎች ህግንና ስርዓትን እንዲሁም ሀገራዊ አንድነትን የሚጠብቁ መሆን እንዳለባቸው ምሁራኑ ተናግረዋል።

ምሁራኑ ከክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት ላይ መሻሻል የሚገባው ነገር እንዳለ አክለው ገልፀዋል። በዚህ ረገድ በክልልሎች ስር የሚተዳደሩ ብሄሮች ውክልናን የሚገልጽ ሕግ በሃገሪቱ ባለመኖሩ ምክንያት እየተነሱ ላሉ ጥያቄዎች መንስኤ ናቸው ተብሏል፡፡

በተለይም በህገ መንግስቱ አንቀጽ 47 ንጹስ አንቀጽ 3 ላይ "ብሄር ብሄረሰቦች በመረጡት ጊዜ ክልል መሆን ይችላሉ" በሚለው ላይ ከአተገባበሩ ጋር በተያያዘ ክፍተት እንዳለው አመልክተዋል።

ከእነዚህም ውስጥ በህዝበ ውሳኔው ላይ የሚሳተፈውን ሰው ቁጥር ለማወቅ የህዝብ ቆጠራ ማድረግ እና የምርጫ ቦርድ በቂ ዝግጅት ማድረግ ተጠቃሽ ናቸውም ተብሏል።