ጠ/ሚ ዐቢይ የፊንላንድና ደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን አነጋገሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የንላንድና ደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ዛሬ ረፋድ ላይ በጽህፈት ቤታቸው አነጋገሩ፡፡

የደቡብ ኮሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካንግ ኪዩንግ ዋ  ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት ደቡብ ኮሪያና ኢትዮጵያ ዘመናትን ያስቆጠረ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በአፍሪካ በሚያደርጉት የመጀመሪያ ጉብኝታቸው ኢትዮጵያን የመጀመሪያ መዳረሻ ማድረጋቸውን የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ ኢትዮጵያ ለደቡብ ኮሪያ ቁልፍ አጋር ሀገር መሆኗን አንስተዋል፡፡

በተለይም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን በደቡብ ኮሪያ ነጻ የትምህርት እድልን እንዲያገኙ እንደሚሰሩም ነው ሚኒስትሯ ካንግ ኪዩንግ ዋ  የተናገሩት፡፡

በሌላ በኩል የፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ሚስተር ፔካ ሀቪስቶ  ሀገራቸው ቀጠናዊ ልማትን ለማጠናከር እንደምትሰራ ገልጸዋል፡፡

በሱዳን የተከሰተውን አለመረጋጋትን በተመለከተም በኢትዮጵያና አፍሪካ ህብረት እየተከናወነ ያለውን እንቅስቃሴ እንደሚያደንቁ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ኢትዮጵያ ያሳየችውን ተነሳሽነት አድንቀው፤ በቀጣይም በሰላም ሂደት ላይ በጋራ ለመስራት ሀገራቸው ቁርጠኛ መሆኗን አስረድተዋል፡፡

በአውሮፓ ህብረት በኩልም በኢትዮጵያ እየታየ ላለው መዋቅራዊ ለውጥ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ በወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ላይም ሀገራቸው ድጋፍ እንደሚያደርግም በንግግራቸው አንስተዋል፡፡

በመጨረሻም የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የነበራቸው ቆይታ ውጤታማና የሀገራቱን ግንኙነት ለማሳደግ ያለመ እንደነበር የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሬስ ሰክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገልጸዋል፡፡