የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ልዩ ስብሰባ ተጠናቀቀ

የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ ባለፉት 10 ቀናት ከሰኔ 28 እስከ ሐምሌ 07/2011 ዓ.ም በአገራዊና ክልላዊ ወቅታዊ የፖለቲካና የጸጥታ ሁኔታዎች እንዲሁም አዳዲስ ክልል ሆኖ የመደራጀት ጥያቄዎች ላይ ሲያካሄድ የነበረውን ስብስባ ማጠናቀቁ ተገለጸ፡፡

ማእከላዊ ኮሚቴው ሀገሪቱ አሁን ያለችበትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት ተወያይቶ የተጀመረው አገራዊ ለውጥ ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ መክሮ አቋም ወስዷል ነው የተባለው፡፡

ክልላዊ አደራጃጀቱን በተመለከተ ዝርዝር ሳይንሳዊ ጥናት ተደርጎ መቅረቡ የተገለጸ ሲሆን፣ ጊዜ ወስዶ በሳል ውይይት ተካሂዶበታል፤ የቀጣይ አቅጣጫም ተቀምጧል ተብሏል፡፡

በተያያዘም የክልሉን ሰላምና ደህንነት አስተማማኝ ማድረግ፣ የህግ የበላይነትን ማስከበር ላይ ጥልቅ ውይይት ተካሂዶ ጠንካራ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

ስለሆነም የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን አጠናክሮ የማስቀጠል፣ የተጀመሩ የለውጥ እንቅስቃሴዎችንና ውጤታቸው ተጠናክረው እንዲሁም የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በጽናትና በመርህ ላይ ቆሞ በመታገል ለላቀ ስኬት እንዲበቃ ማዕከላዊ ኮሚቴው በሙሉ መግባባት ላይ በመድረስ ለቀጣይ ተልዕኮም በቁርጠኝነት መዘጋጀቱን አረጋግጧል ነው የተባለው፡፡ መረጃውን ከደኢህዴን ጽሕፈት ቤት ነው ያገኘነው፡፡