ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አስመራ ገቡ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በኤርትራ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ አስመራ ገብተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እና ልኡካቸው አስመራ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ነው በዛሬው እለት አስመራ የገቡት።

በአስመራ ቆይታቸውም ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በሁለቱ ሀገራት ሁለንተናዊ ትብብር ዙሪ እንደሚመክሩ ይጠበቃል።

በተጨማሪም በሌሎች የሁለትዮሽ ጉዳዮች እና በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋርም የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ወደ አስመራ አቅንተዋል።

በተያያዘ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ የሚያደርገውን በረራ ከጀመረ ዛሬ ድፍን አንድ ዓመት እንደሞላው አስታውቋል።

በቀን ሁለት ጊዜ በአዲስ አበባ እና በአስመራ መካከል በሚያደርገው በረራም እስካሁን 130 ሺህ መንገደኞች ማጓጓዙን ከአየር መንገዱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።