በኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ ህግ ውይይት ህዝብ እንዲሳተፍበት ጥሪ ቀረበ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ ህግ ላይ ተወያይቶ ለማጽደቅ በሐምሌ 15/2011 በአስቸኳይ ስብሰባ ሊሰበሰብ መሆኑን ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡

በዕረፍት ላይ የሚገኘው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ ህግ ላይ ተወያይቶ ለማጽደቅ አስቸኳይ ስብሰባ ይኖረዋል።

በዚህም መሰረት በረቂቅ ህጉ ላይ የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሐምሌ 15/2011 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ላይ ይፋዊ ህዝብ መድረክ አዘጋጅቷል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ በአካል መሳተፍ የሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎች በእለቱ እንዲሳተፉ በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥሪ ቀርቧል።

በአካል መሳተፍ የማትችሉ አካላት ወይም ግለሰቦች ፤ ረቂቅ አዋጁን ላይ ያላችሁን ጥያቄና አስተያየት  በስልክና በኢሜል ማድረስ እንደሚችሉም ተገልጿል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዕረፍት ላይ በሚሆንበት ወቅት በኢፌዲሪ ህገ መንግስት ድንጋጌ እና በተሻሻለው የምክር ቤቱ የአሰራርና የአባላት ስነ-ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀፅ 15(2) መሰረት የምክር ቤቱን አስቸኳይ ውሳኔ በሚሹ ጉዳዮች ላይ አስቸኳይ ስብሰባ ሊጠራ ይችላል፡፡