የአማራ እና የሶማሌ ክልሎች የሕዝብ ለሕዝብ ውይይት ተጀመረ

የአማራና ሶማሌ ክልል ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ የውይይት መድረክ በዛሬው ዕለት በባህር ዳር ከተማ የአማራ ክልል ምክር ቤት አዳራሽ መካሄድ ጀምሯል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ላቀ አያሌው በውይይት መድረኩ የአማራ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብልፅግና ይቆማል እንጅ ከዛ ላነሰ አላማ አይሰራም ብለዋል፡፡

በህዝብ ለህዝብ ውይይቱም በሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ የሚመሩ 100 የሚሆኑ ልዑካንና ከአማራ ክልል ምክር ቤት የተውጣጡ 200 የሚሆኑ አባላት ተሳትፈዋል።

የህዝብ ለህዝብ የውይይት መድረኩ የሁለቱን ክልሎች ህዝቦች ሰላም፣ አንድነት እና ለዘመናት የቆየ አብሮነታቸውን ለማጠናከር ያለመ ነው ተብሏል።

በውይይት መድረኩ በሁለቱ ክልሎች ህዝቦች ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ዙሪያ የሚያተኩሩ ሁለት ጥናታዊ ፅሑፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ነው ።

ባለፉት አመታት በሁለቱ ህዝቦች መካከል የተዛባውን የታሪክ ትርክት ለማስተካከል መድረኩ ሚና እንዳለው ጥናታዊ ጽሁፍ አቅራቢዎች ገልጸዋል፡፡

ልዑካኑ በባህር ዳር በነበራቸው ቆይታ በትናንትናው ዕለት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ምርቃት ስነ-ስርዓት ላይ የታደሙ ሲሆን፣ የጣና ላይ ታሪካዊ ሥፍራዎችንም ጎብኝተዋል።