የአገሪቱ ችግሮች መነሻ በስራ ላይ ያለው ህገ-መንግስት መሆኑን ኢዜማ አስታወቀ

የአገሪቱ ችግሮች መነሻ በተወሰነ ደረጃ አሁን በስራ ላይ ያለው ህገ-መንግስት መሆኑን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ አስታወቀ፡፡

ችግሮቹ በዘላቂነት የሚፈቱት በህገ-መንግስቱ ውስጥ አሉ የሚባሉ ችግሮች ሲሻሻሉ እንደሆነ ፓርቲው እንደሚያምን ነው የገለፀው፡፡

ፓርቲው ዛሬ በአገራዊ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

መግለጫው በደቡብ ክልል እየተነሳ ባለው የክልልነት ጥያቄ እንዲሁም በሰላምና መረጋጋት ላይ ያተኮረ ነው፡፡

ከቀናት በፊት ከሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በዞኑ በሚኖሩ የተለያዮ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ እጅግ አሳዛኝ ጉዳት መድረሱን የገለፀው ፓርቲው በዚህም የሰው ህይወት መጥፋቱን፣ በርካታ ንብረት መውደሙን እና ቤተ-እምነቶች መቃጠላቸውን ተናግሯል፡፡

ድርጊቱን ያወገዘው የፓርቲው መግለጫ ክስተቱ እንደአገር አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሳችንን የሚጠቁም ነው ብሏል፡፡

መንግስት በሲዳማ ዞን የተፈጠረውን ችግር ለማርገብ አፋጣኝ ፖለቲካዊና ህጋዊ እርምጃ መውሰድ አለበት ያለው ኢዜማ፤ በጥፋቱ ውስጥ እጃቸው አለበት የተባሉ አካላትን በማጣራት ለህግ ማቅረብና ለህዝብ ማሳወቅ እንደሚገባው አሳስቧል፡፡

ለተጎጂዎችም ተገቢው ካሳ እንዲከፈል የጠየቀው ፓርቲው በቀጣይ በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ መንግስት የፀጥታ መዋቅሩን በማጠናከር ዜጎችን ከጥቃት የመከላከል ሀላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ፓርቲው በሲዳማ ዞን በተለያዮ ቦታዎች በዜጎች ላይ በደረሰው ጉዳት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በመግለጽ መንግስት ለሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ እንዲሰጥ ከዚያም ለቀጣዮ አገራዊ ምርጫ አስፈላጊውን መደላድል እንዲፈጥር ጠይቋል፡፡ የዘገበው ኢብኮ ነው።