የፖለቲካ ፓርቲዎች ለድርድርና ለውይይት በራቸውን ክፍት በማድረግ ወደ ተቀራረበ ሐሳብ መሰባሰብ እንደሚኖርባቸው ተገለጸ

የፖለቲካ ፓርቲዎች ለድርድርና ለውይይት በራቸውን ክፍት በማድረግ ወደ ተቀራረበ ሐሳብ መሰባሰብ እንደሚኖርባቸው በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አዘጋጅነት በፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረና ውህደት እንዲሁም ትብብር ላይ በተዘጋጀው ስልጠና ላይ ተገለጸ፡፡

የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች በተሳተፉበት ሥልጠና ላይ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሰባሳብና የምርጫ ስርአቱን ግልጽና ከግጭት የራቀ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጠራ ውህደት እንዲፈጥሩ የሚያስችሉ የምርጫ ህጎችም እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡

የስነ-አእምሮ ህክምና ባለሙያው ዶ/ር ምህረት ደበበ በፓርቲዎች ውህደት እና በውድድር ላይ ትኩረት ያደረገ የመነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡ ዶ/ር ምህረት በመነሻ ጽሑፋቸው ፓርቲዎች ወደ ቅንጅት ከማሰራቸው በፊት የትብበር ምሰሶዎችን፣ ህጎችንና ታሳቢ ችግሮችን መለየት እንደሚኖርባቸው ጠቅሰዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ውህደት ለመፍጠር የጋራ ራእይ እሴት እና ግልጽ ዓላማ ሊኖራቸው እንደሚገባ ዶ/ር ምህረት አክለው ገለጸዋል፡፡ በተግባር ምዕራፍ ላይም ሰውን ማዕከል አድርጎ መስራት መዳረሻን ለይቶ ማስቀመጥም የውህደት መነሻ ምሰሶዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከቅርብ ጊዚ ወዲህ በፕሮግራም የሚቀራሩረቡ ፓርቲዎች ውህደት እየፈጠሩ ቢሆንም፣ አሁንም በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለው ጽንፍ የረገጠ መራራቅ ለቁጥር የበረከተውን የፓርቲዎች ቁጥር የፖለቲካ ስርአቱ መሸከም በሚችለው ልክ ማድረግ አላሰቻለም ተብሏል፡፡

በስልጠናው ላይ ለመነሻ የቀረበውን የውህደት ጽንሰ ሀሳብ መነሻ በማድረግ በተሳታፊ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት ተካሂዷል፡፡