የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጦችን በሱማሊኛና በትግሪኛ ቋንቋ ማሳተም ሊጀምር ነው

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በ2012 ዓ.ም በሱማሊኛና በትግሪኛ ቋንቋዎች ጋዜጦችን ማሳተም እንደሚጀምር፤ ዘመናዊ የህትመት ሚዲያ ኮምፕሌክስ እንደሚገነባም የድርጅቱ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ገለፁ።

የአዲስ ዘመን ጋዜጣ 78ኛ ዓመት የምስረታ በዓልና የለውጥ ጋዜጦች ምርቃት ዝግጅት መርሐ ግብር ላይ የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ካሳሁን ጎፌ እንደተናገሩት፣ ድርጅቱ በ2012 ዓ.ም. በሱማሊኛና በትግሪኛ ቋንቋዎች ጋዜጦችን ማሳተም እንደሚጀምር፤በቀጣይም በሌሎች የአገሪቱ ቋንቋዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ተጠቃሽ የህትመት ሚዲያ ኮምፕሌክስ እንደሚገነባ እቅድ ተይዟል።

እንደ ቦርዱ ሰብሳቢ ገለፃ፤ ድርጅቱ በአገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ አስተሳሰብ ወደ ህዝብ በማድረሱ በኩል የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት ሚዛናዊ የሃሳብ ነጻነት የሚስተናገድበት ተቋም ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል። የይዘቱና የቅርጽ ለውጥ ሥራዎቹም አበረታች ውጤት አስገኝተዋል።

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ በበኩላቸው ድርጅቱ አንጋፋ የህትመት ሚዲያ በመሆኑ ባለፉት በርካታ ዓመታት በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ድልድይ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል፤ የሚጠበቅበትን ያህል ውጤታማ ለማድረግ፣ የውስጥ አደረጃጀቱን ለማሻሻል፣ የማተሚያ ቤት ችግሩን ለማስወገድና አሰራሩን ዘመናዊ ለማድረግ ሊጠቀሱ የሚችሉ ጉልህ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

ድርጅቱ በየዘመኑ በርካታ ፈተናዎች እንደነበሩበት ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ የፖቲካ ምህዳር መጥበብ፣ የህትመት ጥራት መጓደልና ተደራሽነት በሚፈለገው ደረጃ አለመሆን፣እንዲሁም የይዘት ጥራት ችግሮችን መፍትሄ ለመስጠት በአሁኑ ወቅት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ ባለፈው አንድ ዓመት ያሉትን ችግሮችን ለመቅረፍ ስልታዊ እንቅስቃሴ በማድረግ የህግ ማሻሻያ ተደርጓል፣ የይዘት ማሻሻያ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፣ድርጅቱ የህትመት ሚዲያ ብቻ ሳይሆን የህትመት ማሳያ ምሳሌ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ነው።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፤ የፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተወካይ፤ ወይዘሮ የሽመቤት ነጋሽ ድርጅቱ ከተቋቋመ ጀምሮ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዜጎች ተሳታፊ እንዲሆኑና በህዝቦች መካከል መቻቻልና መከባበር እንዲኖር አስተዋፅኦ አድርጓል።

ድርጅቱ ተጠሪነቱ ለምክር ቤቱ መሆኑና የተቋቋመበት አዋጅ መሻሻሉን ተጠቅሞ ዘመናዊነትን በመላበስ የሚፈለግበትን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባልም ብለዋል።

ድርጅቱ ባዘጋጀው በለውጥ ጋዜጦች ምርቃት ዝግጅት መርሐ ግብሩ ላይ አንጋፋ ደንበኞቹን ሸልሟል።