የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ጋር በካይሮ ተወያዩ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከግብፁ ፕሬዝደንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ጋር በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በግብፅ ካይሮ ተወያይተዋል።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የተላከ መልዕክት ለግብፁ ፕሬዝደንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ አድርሰዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተመራው ልዑካን ቡድን አሌክሳንደሪያ በሚገኘው ሀራምሌክ ቤተ-መንግሥት ፕሬዝደንት አል ሲሲን አግኝቶ ያነጋገረ ሲሆን፣ በውይይቱ ወቅት ፕሬዝደንቱ የኢትዮጵያ ልዑካን ባደረገው ጉብኝት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸውላቸዋል።

ፕሬዝዳንት አል ሲሲ የግብጽ መንግሥት ለሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች ግንኙነት ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥም አረጋግጠዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል አመስግነው፤ የሁለቱ አገሮች ግንኑነት ይበልጥ በሚጠናከርበት አግባብ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የተላከውን መልዕክት ለፕሬዝዳንቱ አድርሰዋል፡፡

በካይሮ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በደረሱበት ወቅት በግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር አምባሳደር አቡበከር ሄፍኒ፣ በካይሮ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እና በካይሮ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሚሲዮ ሠራተኞች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት