የ2011 በጀት ዓመት የውጭ ዲሎማሲያዊ ተግባራት ስኬታማ እንደነበሩ ተገለጸ

በ2011 በጀት ዓመት የተከናወኑ የውጭ ዲፕሎማሲያዊ ተግባራት ስኬታማ እንደነበሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ የሚኒስቴሩን የ2011 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም አስመልክተው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ የትኩረት አቅጣጫ በሆኑት በኢኮኖሚ እና ዜጋ መር ዲፕሎማሲ፣ የአሜሪካ፣ አውሮፓ፣ እስያ አውስትራሊያ ዓለምአቀፍ ተቋማት እንዲሁም የሚኒሰቴሩ አዲስ የሰው ኃይል ስምሪት አንፃር ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡   

የኢትዮ ኤርትራ የንግድ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የንግድ ስምምነቶች እየተዘጋጁ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል፡፡ የሁለቱን ሀገራት የንግድ ልውውጥ ህጋዊ ማድረጉ በሁለቱ ሀገራት መካከል አሁን ላይ የታየውን ሰላማዊ ግንኙነት የሚያጠናክርና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ይሆናልም ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ ባለፈው በጀት ዓመት ከጅቡቲ፣ ኬንያና ሌሎች የቀጠናው ሀገራት ጋር በቀጠናው ሰላምና በኢኮኖሚው መስክ ዙሪያም ሰፊ ስራ ማከናወኗን ገልጸዋል።

በሱዳን ተፈጥሮ የነበረው ችግር ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለስ ኢትዮጵያ የበኩሏን ድርሻ መወጣቷንም አስታውሰዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ሃይለሚካኤል በበኩላቸው ባሳለፍነው በጀት ዓመት በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲና ቆንስላ ጉዳዮች ዙሪያ ከእቅድ በላይ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ 168 ቢዝነስ ፎረሞች ተዘጋጅተው 1 ሺህ 150 ኩባንያዎች ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፣ 225 ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡

የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ከውጭ ባለሃብቶች ጋር በሽርክና እንዲሰሩ ለማድረግ በተከናወነው ተግባርም 67 ትስስሮች መፈጠራቸውን ጠቅሰዋል።

ያሳለፍነው በጀት ዓመት በተለያዩ ሀገራት በእስር ላይ የነበሩ ከ27 ሺህ በላይ ዜጎች ከእስር ተፈተው ወደ ሀገራቸው የተመለሱበት እንደነበርም ገልጸዋል። በተጨማሪም በውጭ ሀገራት የነበሩና የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው 112 ሺህ 615 ዜጎች ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል ብለዋል፡፡ 

አሁንም ከ4 ሺህ በላይ ዜች በተመሳሳይ ሆኔታ በተለያዩ የውጭ ሀገራት በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን ለማስመለስ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አስገንዝበዋል፡፡

የአህጉራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ማርቆስ ተክሌ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የገቢ አጋር እንደሆኑ የሚገለጽላቸው  የአሜሪካ፣ አውሮፓ እና እስያ አህጉራትና አገራትን ጨምሮ አለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ያለውን የለውጥ ሂደት እንደሚደግፉ የማስገንዘብ ሥራ ተከናውኖ አመርቂ ውጤቶች ተገኝተውበታል፡፡ አገራቱ ለውጡ ተቋማዊ ሆኖ እንዲቀጥል ጠንካራ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ታውቋል፡፡