በአማራ ክልል በሰኔ 15ቱ ጉዳይ የተጠረጠሩ 57 ተከሳሾች ከእስር ተፈቱ

ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በአማራ ክልል በተፈጠረው የከፍተኛ ባለስልጣናት ግድያና ተያያዥ የፀጥታ መደፍረስ ችግሮች የተጠረጠሩ 57 ተከሳሾች ከእስር ተፈቱ።

ተጠርጣሪዎቹ ትናንት በባሕር ዳር ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት 13ኛ ወንጀል ችሎት ለሦስተኛ ጊዜ ቀርበው ጉዳያቸው ታይቶ፥ ከተጠርጣሪዎች መካከል ከወንጀሉ ነፃ የተባሉ 57 ተጠርጣሪዎች እንዲለቀቁ ተደርጓል።

በዚህ መዝገብ 218 ተጠርጣሪዎች የተያዙ ቢሆንም ቀደም ሲል 103ቱ ጉዳያቸው ተጣርቶ መለቃቀቸው ይታወሳል።

ቀሪዎቹ ችሎት ከቀረቡት መካከል ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ማሞ፣ ኮሎኔል አለበል አማረና ኮሎኔል ባምላኩ ዓባይን ጨምሮ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ይገኙበታል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች ኮሎኔል አለበል አማረና ኮሎኔል ባምላኩ ዓባይ እስካሁን ተጨባጭ ማስረጃ እንዳልተገኘባቸው በምርመራ ቡድኑ መረጋገጡን ጠቅሰዋል።

እንዲሁም ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ማሞ የተፈጠረውን ችግር ለመመከት ሲሰሩ የነበሩ መሆናቸውን እየተካሄደ ባለው ምርመራ መረጋገጡንና እስካሁን ማስረጃ አለመገኘቱን ጠበቆቹ አስረድተዋል።

በመሆኑም በስም ተጠቃሾቹ በጉዳዩ የተሳተፉ አለመሆናቸው በተካሄደው ምርመራ እየታየ በመሆኑ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ሳይሰጣቸው መዝገቡ ተዘግቶ እንዲለቀቁ ችሎቱን ጠይቀዋል።

ከተጠርጣሪ እስረኞች መካከል የመቁሰል አደጋ ያለባቸው ተጠርጣሪዎች ስማቸው ተዘርዝሮ ሕክምና እንዲያገኙ ችሎቱ እንዲያዝም ነው ጠበቆቹ የጠየቁት።

ኮሎኔል አለበል አማረ በበኩላቸው “ከታሰርን ጀምሮ አመላካች ውጤት ባለመገኘቱ ቤተሰቦቻችን እየተጎዱ በመሆኑና የመንግሥት ሠራተኞች በመሆናችን ፍርድ ቤቱ ጉዳያችንን በአግባቡ መዝኖ ሊለቀን ይገባል” ብለዋል።

ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ማሞ ደግሞ “ችግሩ እንዳይሰፋና ወደ ከፋ ጫፍ ሁኔታ እንዳይሄድ ያስቆምኩት እኔ ነኝ” በማለት ለችሎቱ ተናግረዋል።

“እስካሁን በምርመራ መዝገቡም ማስረጃ ማቅረብ አልተቻለም፤ ምንም በሌለ ጉዳይ መታሰሬ አግባብ ባለመሆኑ ልለቀቅ ይገባል” ሲሉም ችሎቱን ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ የተጠርጣሪዎች ጉዳይ በጥንቃቄና በፍጥነት እየታየ ነፃነታቸው የተረጋገጠላቸው እየተፈቱ መሆኑን ለችሎቱ አስረድቷል።

ይሁን እንጅ ከታሰሩት መካከል ቀጥታና በተዘዋዋሪ የተሳተፉ እንዲሁም ከችግሩ ነፃ የሆኑ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ በመጥቀስ፥ ጉዳዩ በሰውና በቴክኒክ ማስረጃ እንዲጣራ ተደርጎ ከወንጀሉ ንጹህ የሆኑ ሰዎች እንደሚፈቱ አስታውቋል።

“ከጉዳዩ ነፃ የሆኑ ሰዎችን በምንም መንገድ ቢሆን አላግባብ የሚወነጅል የለም፤ ማጣራቱ ለተጠርጣሪዎችም ቢሆን ጠቀሚ ነው” ብሏል ፖሊስ።

በመሆኑም እስካሁን ያልተጣሩና መጣራት ያለባቸውን ጉዳዮች በሰውና በቴክኒክ ማስረጃ ለማጣራት የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው መጠየቁን የአማራ ብዙሃ መገናኛ ድርጅት ዘግቧል፡፡