የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክርቤት የስራ ዘመን የሚያበቃበት ቀነ ገደብ አስካልተቀመጠ ድረስ ስራውን እንደሚቀጥል ገልጿል፡፡
ምክር ቤቱ በኦዲት ግኝት ከተያዙ 42 ተቋማት የሰበሰበውን 50 ሚሊየን ብር ለመንግስት ገቢ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ምክር ቤቱ 6ኛ አመት 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን ከሐምሌ 25 እስከ 27፣ 2011 ዓ.ም እንደሚያካሂድም ነው የገለፀው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የስራ ዘመን 2010 ላይ መጠናቀቁን ተከትሎ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምክር ቤቱን የስራ ዘመን ላልተወሰነ ጊዜ ማራዘሙ ይታወሳል፡፡
ይህንኑ ጉዳይ በሚመለከት በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችን ተጨባጭ መረጃ ከሌላቸው አካላት የምክር ቤቱ የስራ ዘመን ሰኔ 30/2011 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ የሚሰራጨው መረጃ ስህተት መሆኑን የምክር ቤቱ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አዲስአለም እንቻለው ገልጸዋል፡፡
የምክር ቤቱ የስራ ዘመን የሚያበቃበት የጊዜ ገደብ እስካልተቀመጠ ድረስም ምክር ቤቱ ስራውን እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት፡፡
ምክር ቤቱ የፋይናንስ ስርዓቱ በሚፈቅደው መልኩ በጀቱን እየተጠቀመ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ፣ በጀቱ እንደጸደቀ ወደ መደበኛ ስራው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡