ኢህአዴግ ምርጫው ጊዜውን ጠብቆ እንዲካሄድ አቋም አለው – ጠ/ሚ ዐቢይ

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሀገራዊ ምርጫው ጊዜውን ጠብቆ እንዲካሄድ አቋም እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በዛሬው እለት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን፥ ከጥያቄዎቹም ከምርጫ ጋር የተያያዘው አንዱ ነበር።

በዚህም በሰጡት ምላሽ በአሁኑ ወቅት ምርጫ ይራዘም የሚሉ እና ወቅቱን ጠብቆ ይካሄድ የሚሉ የራሳቸው ምክንያት ያላቸው አካላት እንዳሉ አንስተዋል።

ነገር ግን የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባው ምርጫ ከማካሄድ ጋር በተያያዘ በዝርዝር እንደተወያየበትና ምርጫው አይደረግም የሚል አቋም እንደሌለው አስታውቀዋል።

ኢህአዴግ ምርጫው ጊዜውን ጠብቆ እንዲካሄድ አቋም አለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ለዚህም በቂ ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም አያይዘው ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጂ ኢህአዴግ ምርጫው ይካሄድ የሚለው ላይ ብቻውን ውሳኔ ማሳለፍ አይችልም ያሉ ሲሆን፥ ሁሉን የፖለቲካ ፓርቲዎች በማሳተፍና በህዝቡ ይሁንታ የምርጫው ሁኔታ ላይ ከስምምነት በመድረስ እንደሚከናወንም አብራርተዋል።

ከዚህ ጋር አያይዘውም አዲስ የምርጫ ህግ እየተዘጋጀ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ህጉ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሚመለከታቸውን አካላት ባሳተፈ መልኩ መዘጋጀቱን አንስተዋል።

የህወሃትና አዴፓ መግለጫዎች በተመለከተ፣

ሰሞኑን በህወሃትና በአዴፓ መካከል ባለው ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ ለቀረበላቸው ጥያቄም፥ ህወሃትና አዴፓ በየፊናቸው ያወጡት መግለጫ በፖለቲካው ዓለም የሚያጋጥም መሆኑን አንስተዋል።

ሁለቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለረጅም ዓመታት ለህዝብ ጥቅም ሲሉ አብረው ታግለዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክትር አብይ፥ በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ ግን እንዲህ አይነት ንትርኮች አልታጡም ብለዋል።

አሁንም በህወሃትና አዴፓ መካከል የተፈጠረው ነገር የሚያጋጥም መሆኑን በማንሳት፥ መግለጫው ግን በዚያ መንገድ ባይሆን ይመረጥ እንደነበረ አንስተዋል።

ነገር ግን ጥይት እስከሌለው ድረስ በፖለቲካ ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች አስደንጋጭ ሊሆኑ እንደማይገባም ነው ያስታወቁት።

በቀጣይም የመግለጫ ምልልሱን እንዴት እንፍታው የሚለው ላይ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ትኩረት ሰጥተውበት እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ሁለቱ ድርጅቶች ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ መድረክ እንደሚዘጋጅ አስታውቀዋል።

የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ውህደትን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ውህደቱን በተመለከተ ጥናት ሲደረግበት እንደቆየ እና ወደፊትም ሰፋፊ ውይይቶች እንደሚካሄዱበት ጠቅሰዋል።

ከእህት ድርጅቶች ዘንድ ከውህደቱ በፊት መስተካከል አለባቸው በሚል የተነሱ ነጥቦች እንዳሉ በመጠቆም፤ ነገር ግን ውህደቱን መቀበል የማይፈልጉ ፓርቲዎች አሉ በሚል መውሰድ አይገባም ብለዋል።

ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር ተያይዞም ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ተቀባይነት እንደነበረ አሁን ግን እየተሸረሸረ መጥቷል በሚለው ለቀረበላቸው ጥያቄም፥ ተቀባይነት እንደነበረ አሁን ግን እየተሸረሸረ መጥቷል በሚለው በማስረጃ የተደገፈ አይደለም ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ እንደማሳያ መቅረብ እንደሌለበትና፤ ዳያስፖራው ለሀገሩ ሲል ትረስት ፈንዱን መደገፍ እንዳለበት ተናግረዋል።

አሁንም ቢሆን ከሰብአዊ መብት አያያዘ ጋር ከለውጡ ወዲህ ወደኋላ የተመለሰ ነገር እንደሌለና እሳቸውም ይሁን ሀገርን የሚመራው ድርጅት በሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ተመሳሳይ አቋም እንዳላቸው ገልፀዋል።

ከህግ ማስከበር ጋር ተያይዞ ሁሉም ህግ ይከበር ይላል እንጂ የራሱን ወንጀለኛ አሳልፎ ለመስጠት ፍቃደኛ አይደለም ያሉ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት ህግ ይከበር በሚል የሚነሱ ቅሬታዎች እንደ ቂም መወጣጫ እየተቆጠሩ መምጣታቸውን አንስተዋል።

ይሁን እንጂ መንግስት ህግ መከበር አለበት የሚል አቋም እንዳለው እና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጠል አስታውቀዋል።

ከኢኮኖሚው አንፃርም በተለይም ከውጭ ምንዛሬ አንፃር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከዚህ በፊት ከነበሩ ዓመታት በተሻለ ገቢ መግባቱን በመጥቀስ፤ ነገር ግን የፍላጎት መጨመር ክፍተት ፈጥሮ እንደነበረ አስታውሰዋል።

በውጭ ምንዛሬ ረገድ የተሰራውን ስራ በማጠናከር ችግሮቹን መቅረፍ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ በተመለከተ፣

የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄን በተመለከተም፤ ክልል የመሆን ጥያቄው ለረጅም ዓመታት የነበረ መሆኑን እና ከለውጡ በኋላ ጎልቶ መውጣቱን አንስተዋል።

የክልልነት ጥያቄው ከፖለቲካ በተጨማሪ የሀብት ክፍፍል እና ህጋዊ ሂደቶች ያስፈልጉታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ የክልልነት ጥያቄውን መሰረት በማድረግ ህዝበ ውሳኔው ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንደሚከናወንም አስገንዝበዋል።

ከችግኝ ተከላ ጋር በተያያዘ ህዝቡን በድጋሚ በማመስገን በቀጣይም ህዝቡ በተከላው ያሳየውን ርብርብ ችግኞቹን ተንከባክቦ ማሳደግ ላይ እንዲደግመውም ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የችግኝ ተከላውን ለማስፈጸም የተቋቋመው አብይ ኮሚቴ የተተከሉ ችግኞችን የመከታተል ስራ እና ለቀጣይ ዓመት ችግኝ ተከላ ከወዲሁ ሰፋፊ የቅድመ ዝግጀት ስራዎችን ቀጥሎ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።