በአረንጓዴ አሻራ የታየው አንድነት በሌሎች መስኮችም ይደገማል- ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ

ከሰሞኑ በችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ህዝቡ ያሳየውን አንድነት በቀጣይ ዓመት በተለያዩ መስኮች ለመድገም መታሰቡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ገለፁ፡፡

መንግስት ህዝቡ በችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እንዲሳተፍ ያደረገውን ጥሪ ተከትሎ ለሰጠውን መልካም ምላሽ ያመሰገኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በቀጣይም ይህን ተግባር በሌሎች መስኮች ለመድገም ዝግጅት መኖሩን አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ለጋዜጠኞች የሰጡት ማብራሪያ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ባጠነጠነው ማብራሪያቸው ኢህአዴግ ወደ ውህድ ፓርቲ ለመምጣት ጥናቶች እያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከሰላምና ፀጥታ ጋር በተያያዘ የህግ የበላይነትን ለማስከበር መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ነው በመግለጫቸው የጠቆሙት፡፡

ከሰኔ 15 ጥቃት በኋላ መንግስት የዜጎችን ድምፅ ለማፈን ጥረቶችን እያደረገ ነው ተብሎ ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄም መንግስት ድምፅ ለማፈን ፍላጎት እንደሌለው በመልሳቸው አንስተዋል፡፡

ከመፈንቅለ መንግስቱ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለው ከነበሩት መካከል 120 ያህሉ መፈታታቸውንና በድርጊቱ ተሳትፈዋል ተብሎ የተጠረጠሩትንም በማጣራት የመፍታት ሂደት ይቀጥላል ብለዋል።

የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በመንግስት በኩል ጥረቶች እየጸደረጉ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አስተማማኝ የህግ ማስከበር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸውና ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ማህበራዊ ይዘት ባላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡