ኮማንድ ፖስቱ በደቡብ ክልል የሚታዩ ህገ-ወጥ አርማዎችና ምልክቶች በአስቸኳይ እንዲነሱ አሳሰበ

በደቡብ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ የተሰቀሉ ህገ-ወጥ ታፔላዎችና ምንነታቸውና ማንነታቸው የማይታወቅ አርማዎች በሁለት ቀናት ውስጥ እንዲነሱ የክልሉ ጊዜያዊ የጸጥታ ኮማንድ ፖስት አሳሰበ።

ኮማንድ ፖስቱ ትናንት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው በቅርቡ በሀዋሳ ከተማና ሲዳማ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ሁከትና ብጥብጥ መከሰቱን ተከትሎ በሌሎች ዞኖችም የተለያየ መገለጫ ያላቸው ህገ-ወጥ ድርጊቶች መፈጸማቸውን አመልክቷል።

የክልሉ መንግስት ህጋዊ ሰንደቅ ዓላማ ከመንግስት ተቋማት ከግል ድርጅቶችና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጭምር ወርደው በምትኩ በአንዳንድ አካባቢዎች ህጋዊ ያልሆኑና የማን እንደሆኑ በህግ የማይታወቁ አርማዎች መሰቀላቸውን አስታውቋል።

በአንዳንድ ዞኖችም ህጋዊ የመንግስት ተቋማትን ምንነትና አድራሻ የሚገልጹ ምልክቶችና ታፔላዎች በህገ-ወጥ መንገድ መነሳታቸውን ያመለከተው መግለጫው ይህንን ተከትሎ በበርካታ አካባቢዎች ስርዓት አልበኝነት እየተፈጠረ የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት አደጋ ውስጥ እንደከተተ ተጠቁሟል።

የዜጎችን ሰላምና ደህንነት እንዲሁም ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ማስጠበቅ የመንግስት ተቀዳሚ ተግባር በመሆኑ ከሐምሌ 29 እስከ 30/2011 ባሉት ሁለት ቀናት ውስጥ ችግሮቹን የፈጠሩ ህገ-ወጥ ተግባራት ባስቸኳይ እንዲስተካከሉ ኮማንድ ፖስቱ መመሪያ አስተላልፏል።

በዚህ መሰረትም ህጋዊው ሰንደቅ ዓላማ በመንግስትም ሆነ መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት እንዲሰቀል ከማድረግ ጀምሮ በየትኛውም የክልሉ አካባቢ በህጋዊ-መንገድ ያልተፈቀደ አርማም ሆነ ሌላ ምልክት ይዞ መንቀሳቀስ መከልከሉን አስታውቋል።

በተለያዩ የህትመት ውጤቶች የተዘጋጁ ህገ-ወጥ ምልክቶችና አርማዎች በተለያዩ መንገዶች ይዞ ወይም ለብሶ መገኘት የተከለከለ መሆኑን ያመለከተው መግለጫው በክልሉ ሁሉም መዋቅሮች ህጋዊ የመንግስትና የድርጅት ተቋማትን ምንነትና አድራሻ የሚገልጽ ትክክለኛ ጽሁፍና ታፔላ በግልጽ እንዲሰቀል አሳስቧል።

በሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ከተማ አስተዳደሮች ወረዳዎችና ቀበሌዎች የተቋማትም ሆነ ድርጅቶች እንዲሁም በአደባባይና በመንገድ ዳር የሚሰቀሉ ህገ-ወጥ የመንገድ ዳር ባነሮች ታፔላዎችና ምልክቶች በአስቸኳይ እንዲነሱ ማዘዙንም የኮማንድ ፖስቱ መግለጫ ያመለክታል።

ህጋዊ የሆኑ ጉዳዮችን በቦታው የመመለስና ህገ-ወጥ የሆኑትን የማንሳት ስራው በተቀመጠው ጊዜ የማይተገበር ከሆነ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ አስፈላጊውን የማስተካከያ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ የክልሉ ጊዜያዊ የጸጥታ ኮማንድ ፖስት አስታውቋል። (ምንጭ:-ኢዜአ)