የዴሞክራሲ እሴቶችን በማስረጽ የሚዲያ ተቋማት ሚና ዝቅተኛ ነበር ተባለ

ባለፉት 20 አመታት ዴሞክራሲን በማስረፅ ረገድ የህዝቦችን ተሳትፎ የቃኘ ጥናት ይፋ በሆነበት ወቅት እንደተገለፀው፤ በርካታ የሚዲያ ተቋማት የዴሞክራሲ እሴቶችን አጉልቶ በማውጣት ረገድ ሰፊ ውስንነቶች ታተውባቸዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በርካታዎቹ  የስነ-ምግባር መርሆዎችን ሳይጠብቁ  የመዘገብ ዝንባሌ ነበራቸው ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢኒስቲትዩት በተካሄደውና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ ዜጎች በተሳተፉበት አውደ ጥናት በዋናነት በዴሞክራሲ ስርፀት ዙሪያ የዜጎችን ምልከታ፣ አተገባበርና ተፅእኖን በመገምገም መፍትሄን ማመላከት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ሙሉ በሙሉ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ትኩረቱን ባደረገው በዚህ ጥናት ፖለቲከኞች ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በማተኮር ሀሳብ ከማመንጨት ይልቅ በግላዊ ጥቅሞቻቸው ላይ ማተኮራቸው ሀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዳይወጡ ማድረጉ ተነስቷል፡፡

ዜጎችም ቢሆኑ  ነገሮችን በሰከነ ሁኔታ ከማጤን ይልቅ በስሜታዊነት ወደ አላስፈላጊ ግጭቶች የማምራት ሁኔታ ሲስተዋልባቸው እንደነበር ያመላከተው ጥናቱ፤ ይህም ዴሞክራሲ ስር እንዳይሰድ የራሱን ተፅዕኖ ማሳደሩን ተነስቷል፡፡

በመንግስት በኩል የታዩ ክፍተቶችንም ጥናቱ ያመላከተ ሲሆን፤ በተለይም ለአሰራር ምቹ ያልሆኑ አደረጃጀቶችን ያለመተቸት ችግር፣ በፓርቲዎች የግል አቋም ጣልቃ መግባትን ጨምሮ የዴሞክራሲ ተቋማትን ተናበውና ተቀናጅተው እንዲሰሩ ያለማድረግ ችግሮች ተስተውለዋል፡፡

በመሆኑም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለዴሞክራሲ ስርፀጥ ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ በመድረኩ ጥሪ ቀርቧል፡፡