ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ነሐሴ 11 ቀን 2011 ወደ ሱዳን ካርቱም በመጓዝ በወታደራዊ የሽግግር ሸንጎና በነፃነትና ለውጥ ኃይሎች መካከል የተደረገውን የመጨረሻውን የስምምነት ፊርማ ተከታተሉ::
ይህ የመጨረሻው ስምምነት ወታደራዊ ያልሆነ መንግስት ለመመስረት መንገድ ከፋች ነው ተብሏል::
ከስምምነት ፊርማው ቀደም ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከነፃነትና ለውጥ ኃይሎች አባላት ጋር ተወያይተዋል:: አባላቱ ኢትዮጵያ ለዚህ ስምምነት መፈረም የተጫወተችውን ሚና በማድነቅ እነዚህ ሕገ መንግስታዊና ፖለቲካዊ ስምምነቶች ለዘላቂ ዴሞክራሲያዊና ልማት መሰረት ይጥላል ብለዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው፣ ይቅርታንና አንድነትን በመንከባከብ እንዲተጉ በማበረታታት ስኬታማ ውይይት መልካም መነሻ እንጂ ብዙ ስራ የሚጠይቀው መንገድ ከዚህ ቀጣዩ ነው ብለዋል::
ሴቶች በፖለቲካ አመራር ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ለዚህም አካታች እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በተያያዘም የኢትዮጵያን ልምድ በማንሳት የነፃነትና የለውጥ ኃይሉ ይህንን 50-50 የፆታ አካታች ካቢኔ እንዲተገብሩ አስታውሰዋል::
በሱዳን ስምምነት ፊርማው ስነስርዓት በማስከተል ባደረጉት ንግግር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሀገሪቱ በሚደረገው የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ወቅት የሱዳን ህዝቦች የሰላማቸውና የክብራቸው ተንከባካቢዎች እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል::
በሱዳን ጉዞአቸው ማብቂያም ከመቶ በላይ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወደሌላ ሀገር ለመሻገር ሱዳን የቀሩ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ይዘው ተመልሰዋል:: ከነዚህም ውስጥ በተለያየ ጥፋት እስር ቤት የነበሩም ይገኙበታል ነው የተባለው፡፡ መረጃው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ነው፡፡