በነብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ የክስ መዝገብ ላይ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ

በእነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ የክስ መዝገብ ላይ የምርመራ ቡድኑ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በጠየቀው ይግባኝ ላይ የባሕር ዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ለመስጠት ለነሐሴ 16/2011 አ.ም የጊዜ ቀጠሮ ሰጠ።

በእነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ የክስ መዝገብ ላይ ሐምሌ 29/ 2011 ዓ.ም በነበረው የጊዜ ቀጠሮ የባህር ዳር ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል ። ይህን ተከትሎም የምርመራ ቡድኑ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው የባህር ዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ዛሬ ጠይቋል።

የምርመራ ቡድኑ “አዳዲስ ተከሳሾች ተይዘዋል። ቃል እየተቀበልን ነው። በድርጊቱ ዋና ተከሳሾች ካልተያዙ ክስ መመስረት አንችልም። በህክምና ላይ ያሉትን ምስክሮች ቃል የመቀበል ስራ እየተከናወነ ነው። በፌዴራል ከሚካሄደው ምርመራም ጋር የሚያያዙ ጉዳዮች አሉ። የቀዳሚ ምርመራ የሚሰሙ ብዙ ምስክሮች እያሉን የቀረቡት ጥቂቶቹ ናቸው” በሚሉ ምክንያቶች ተጨማሪ የይግባኝ ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተከሳሾቹ ጠበቆች በበኩላቸው የጊዜ ቀጠሮው ይግባኝ የሚቀርብበት እንዳልሆነ እና ለምርመራ የተሰጠው የጊዜ ቀጠሮ በቂ መሆኑን በመግለጽ ይግባኙን ተቃውመዋል።

ከፍተኛ ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ካደመጠ በኋላ በይግባኝ ክርክሩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለነሐሴ 16/2011 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ቀጠሮ ሰጥቷል።

(ዘገባው የአብመድ ነው)