አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም የደረሱትን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረቡ

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም የደረሱትን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ በማድረግ ወደ ተጨባጭ እንቅስቃሴ እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል።

ሚኒስትሩ ጥሪያቸውን ያቀረቡት የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ፓርቲዎቸ ከዚህ ቀደም የደረሱትን የቅድመ ሽግግር የሰላም ስምምነት አፈፃፀም ሂደት ለመገመገም የተጠራው ስብሰባ ዛሬ አዲሰ አበባ በሚገኘው ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በተጀመረበት ወቅት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ነው።

የቅድመ ሽግግር ጊዜው የደቡብ ሱዳን ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በተገኙበት እኤአ ሜይ 12 ቀን 2019 ዓም በአዲስ አበባ ባደረጉት ውይይት በደረሱት ስምምነት መሰረት እስከ ኖቬምበር 2019 ዓም ድረስ ለ6 ወራት ያህል መራዘሙ ይታወቃል።

ስምምነቱ እንዲራዘም መግባባት ላይ ከተደረሰ ጊዜ አንስቶ ወደ ሌላ አገር የተሰደዱ የደቡብ ሱዳን ህዝቦች እና ተቃዋሚ ሃይሎች ወደ ጁባ በመመለስ መኖር መጀመራቸው በፓርቲዎች መካከል መተማመን የፈጠረ መሆኑን እንዲሁም በደቡብ ሱዳን ያለው ግድያ እና ተኩስ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ በደቡብ ሱዳን ሰላምን ለማስፈን አበረታች ጅምር መሆኑን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ተግባራዊ መደረግ ያለባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ማለትም የጋራ የፀጥታ ሃይል ምስረታ፣ የሰው ሃይል ስልጠናና ስምሪት፣ የክልላዊ መንግስታትን ቁጥር የመወሰንና መስል ስራዎች አፈፃፀም አዝጋሚና ዝቅተኛ መሆኑን በማስታወስ ሁሉም ፓርቲዎች ለደቡብ ሱዳን ህዝብ ጥቅም ሲሉ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ እንዲሆኑ ክቡር ሚኒስትሩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በዛሬው ውይይት የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የኢጋድ አባል አገራት፣ የኢጋድ ባለድርሻ አካለት ፎረም፣ የትሮይካ፣ የቻይና፣ የውሮፓ ህብረት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካለት ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

ስብሰባው በደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ፓርቲዎች የተደረሰውን ስምምነት ተግባራዊ ለማደረግ የተሰሩ ስራዎችን ሪፖርት በማዳመጥ እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማመላከት በዛሬው እለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል። መረጃው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽ/ቤት ነው፡፡