ም/ቤቱ ባካሄደው 73ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

ም/ቤቱ ባካሄደው 73ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

ምክር ቤት በቅድሚያ በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ተዘጋጅተው በቀረቡ ከፍተኛ ደረጃ የድንጋይ ከሰል ማዕድን እና አነስተኛ ደረጃ የክሮማይት ማዕድን ማምረት ፈቃድ ስምምነቶች ላይ የተወያየ ሲሆን፤ ስምምነቶቹ በህጉ መሰረት መሟላት የሚገባቸው ጉዳዮች ከተሟሉ በኋላ እንደተዘጋጁ ተገልጿል፡፡

ምክር ቤቱም በቀረቡት የከፍተኛ እና የአነስተኛ ደረጃ የማዕድን ማምረቻ ፈቃድ ስምምነቶች ላይ ከተወያየ በኋላ በስራ ላይ እንዲውሉ መወሰኑ ተመልክቷል፡፡

በመቀጠልም ምክር ቤቱ በሰው የመነገድና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፤ በዚህ ዙሪያ የሚደርሱ ወንጀሎች በዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ወንጀሎቹን ለመከላከል የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ለውሳኔ አቅርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ ማሻሻያዎችን በማዕከል ይፀድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡

እንዲሁም የማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን የተለያዩ የማሪታይም አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያወጣውን ወጪ ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ የአገልግሎቱ ቀጥተኛ ተጠቃሚ የሆነው ተገልጋይ እንዲሸፍን ለማድረግ የሚያስችል የህግ መሰረት መኖሩ አስፈላጊ መሆኑን በመግለፅ፤ የገንዘብ ሚኒስቴር የአገልግሎት ክፍያውን ለመወሰን የሚያስችል ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ያቀረበ ሲሆን፤ ምክር ቤቱም ደንቡ ላይ ተወያይቶ በስራ ላይ እንዲውል መወሰኑን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡