ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከደቡብ ኮርያ ፕሬዝዳንት ሙን ጃ-ኢን ጋር ተገናኝተው ተወያዩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከደቡብ ኮርያ ፕሬዝዳንት ሙን ጃ-ኢን ጋር ተገናኝተው ተወያዩ::

በውይይታቸው ወቅት ፕሬዝዳንት ሙን ጃ-ኢን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እየወሰዱ ያሉትን መልካም እርምጃዎች በማድነቅ መላው አለም እየተመለከተ እንዳለ አንስተዋል::

መሪዎቹ  በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ የተስማሙ ሲሆን ከውይይቱም በተጨማሪ ሁለቱ ወገኖች የተለያዩ ስምምነቶችና የመግባቢያ ሰነዶች ተፈራርመዋል::

በዚህም መሰረት በአምስት የተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የመግባቢያ ሰነዶችን ነው የፈረሙት፡፡

1. የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማቲክ ፖስፖርት ይዘው ለሚጓዙ ዜጎች ያለ ቪዛ የሚገቡበት ስምምነት:

2.በሁለቱ ሀገራት መካከል የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ለማቋቋም የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ:

3. በደረጃ፣ ብቃት ማረጋገጫ፣ ተስማሚነት ምዘናና የቴክኒክ ቁጥጥር ዙሪያ በትብብር ለመስራት የሚያስችል የስምምነት ሰነድ፣
4. የአካባቢ ጥበቃ ትብብር የስምምነት ሰነድ እና

5. በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የልህቀት ማዕከልን ለማቋቋም የብድር ስምምነት ናቸው::

ማምሻውን ፕሬዝዳንት ሙን ጃ-ኢን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለማክበር የእራት ግብዣ ያደረጉላቸው ሲሆን፣ ሁለቱም መሪዎች የኢትዮጵያና የኮርያን ህዝቦች ረጅም ታሪካዊ ግንኙነቶች ዙሪያ ንግግር አድርገዋል:: መረጃው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ነው፡፡