አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በቲካድ የሚኒስትሮች ጉባዔ  እየተሳተፉ ነው

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በቲካድ የሚኒስትሮች ጉባዔ ላይ እየተሳተፉ ነው።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሚመራ የልዑካን ቡድን እ.አ.አ ከነሃሴ 28 እስከ 30 ቀን 2019 በዮኮሃማ (ጃፓን) ለሚካሄደው የቲካድ የመሪዎች ስብሰባ በሚኒስትሮች ደረጃ በሚመክረው የአፍሪካ የሚኒስትሮች ጉባዔ ላይ ይሳተፋል።

ከዚሁ ጉባዔ አስቀድሞ የከፍተኛ ባለሙያዎች ስብሰባ ከነሃሴ 25 እስከ 26 ቀን 2019 የተካሄደ ሲሆን፤ በሚኒስትሮች ጉባዔ የሚዳብረውንና በመሪዎች ደረጃ በሚጸድቀው የዮኮሃማ ረቂቅ ሠነድ ላይ ውይይት ተደርጓል።

የዘንድሮው ጉባዔ መሪ ቃልም “የአፍሪካን ልማት በሰው ሃብት፣ በቴክኖሎጂ፣ በፈጠራ ማራመድ” የሚል መሆኑ ተገልጿል።

ከዚሁ የቲካድ ስብሰባ ጎን ለጎን ነሃሴ 30 በሚካሄደው ኢትዬ-ጃፓን ቢዝነስ ፎረምና ኤግዚቢሽን 180 የጃፓን ባለሃብቶች ይገኛሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ 43 የኢትዮጵያ የንግድ ማህበረሰብ አባላትም ይሳተፋሉ።

በአፍሪካ ልማት ዙሪያ ምክክር የሚያደርገው የቶኪዮ አለም አቀፍ ኮንፈረንስ/ ቲካድ/ እ.አ.አ ከ1993 ጀምሮ አፍሪካ ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ በጃፓን ጠንሳሽነትና አመራርነት የሚካሄድ ነው።

በጥምር አዘጋጅነትም የአለም ባንክ፣ የተመድ ልማት ድርጅት እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እየተሳተፉ መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።