ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ከጃፖን ጠቅላይ ሚኒስትር ሽንዞ አቤ ጋር ተወያዪ።

ሁለቱ መሪዎች የሀገራቱን ግንኙነት ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ነው የተወያዩት።

ጠ/ሚ/ር ዐብይ በውይይቱ በኢትዮጵያ እየተከናወነ ስላለው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ተምረውና ሰልጥነው የሚገኙ ወጣቶች በጃፓን ገብተው ስራ የሚሰሩበት ሁኔታ እንዲመቻች መጠየቃቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት የውጭ ቋንቋና ዲጅታል ሚዲያ ሃላፊ ቢልለኔ ስዮም ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በመተግበር ኢትዮጵያን በአፍሪካ ከአምስት በኢኮኖሚ እድገት ቀዳሚ ሀገር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንኑ እውን ለማድረግና የጃፖን የንግዱ ማኅበረሰብም በግብርና: ቱሪዝም: አይሲቲና በማእድን ማውጣት ሥራ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል::

ሽንዞ አቤ የዐቢይን የሀገር ውስጥ የለውጥ አጀንዳ እንደሚደግፉ ገልፀዋል:: እንዲሁም ኢትዮጵያ በኤርትራ የምታደርገውን የሰላም ድጋፍ: በደቡብ ሱዳን ያለውን የሰላም ውይይትና በሱዳን ስምምነት የጠ/ሚር ዐቢይ አሕመድን ሚና ተደናቂ እንደነበር አንስተዋል::

ለጠ/ሚር ዐቢይ አሕመድና ለኢትዮጵያ በተለይም ለጅማ ጭዳ መንገድ ግንባታ ጃፓን የምታደርገውን እርዳታ እንደምትቀጥል ጠ/ሚር ሺንዞ አቤ ተናግረዋል:: ጃፓን አሁን በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ሪፎርም እንደሚደግፉም ገልጸዋል።

በቅርቡ ለሀገራዊ ምርጫ ማስፈፀሚያ ድጋፍ ያደረገችው ጃፓን በቀጣይም ድጋፏን በምትቀጥልበት ሁኔታ መወያየታቸውንም የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት የውጭ ቋንቋና ዲጅታል ሚዲያ ሃላፊ ቢልለኔ ስዮም ገልፀዋል።እንዲሁም በመሰረተ ልማትም በኩል ጃፓን የምታደርገውን ድጋፍ ትቀጥላለች ተብሏል።